ሚክያስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሰላም የሚሰፍንበት የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚመጣ ( ኢሳ. 2፥1-4 ) 1 የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ፥ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተሠራበት ተራራ ከሌሎች ተራራዎች ሁሉ በልጦ ይታያል፤ ከኰረብቶችም ሁሉ እጅግ ከፍ ይላል፤ የብዙ መንግሥታት ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። 2 ስለዚህ ብዙ ሕዝቦች እንዲህ ይላሉ፥ “ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ስለሚገኝ፥ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ እንውጣ፤ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤተ መቅደስም እንሂድ፤ እርሱ ፈቃዱን እንድናደርግ ያስተምረናል፤ እኛም በእርሱ መንገድ እንሄዳለን።” 3 እርሱ በብዙ ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ በቅርብና በሩቅ ባሉ ታላላቅ መንግሥታት መካከል ያለውን አለመግባባት ያስወግዳል፤ ስለ ሆነም ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥ ጦራቸውንም ወደ ማጭድ ይለውጣሉ፤ መንግሥት በመንግሥት ላይ ጦርነት አያነሣም፤ ከዚያ በኋላም የጦር ትምህርት የሚማር አይኖርም። 4 እያንዳንዱ ሰው በተከለው ወይንና በለስ ጥላ ሥር በሰላም ያርፋል። የሚያስፈራውም ነገር አይኖርም፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። 5 አሕዛብ ሁሉ እያንዳንዳቸው ጣዖቶቻቸውን ያመልካሉ፤ እኛ ግን አምላካችንን እግዚአብሔርን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እናመልካለን። የእስራኤል ሕዝብ ከስደት መመለስ 6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያ ቀን አንካሶችንና እኔ ስለ ቀጣኋቸው ተሰደው መከራ የደረሰባቸውን ሕዝቤን እሰበስባለሁ። 7 አንካሶች ተርፈው እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ተጥለው የነበሩትን ብርቱ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔም በጽዮን ተራራ ላይ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በእነርሱ ላይ እነግሣለሁ።” 8 አንቺ የጽዮን ተራራ የመንጋው መጠበቂያ ግንብ ሆይ! የተሰጠሽ ተስፋ ይፈጸማል፤ የቀድሞ ሉዐላዊነትሽ ኢየሩሳሌምም ዋና ከተማነቷ ይመለስልሻል። 9 እንደዚህ ከፍ አድርገሽ የምትጮኺው፥ ምጥ እንደ ያዛት ሴት የምትጨነቂው ለምንድን ነው? ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ አማካሪዎችሽ ሁሉ ስለ ጠፉ ነውን? 10 የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ምጥ እንደ ያዛት ሴት እየቃተታችሁ ተንፈራፈሩ፤ ከከተማ ተባራችሁ በሜዳ ላይ ትሰፍራላችሁ ወደ ባቢሎንም ትሄዳላችሁ፤ ይሁን እንጂ በዚያ እግዚአብሔር ያድናችኋል፤ ከጠላቶቻችሁም እጅ ይታደጋችኋል። 11 አሁን ግን ብዙ ሕዝቦች በእናንተ ላይ ተሰብስበው እንዲህ ይላሉ፦ “ኢየሩሳሌም ትርከስ! እኛም መፍረስዋን እንይ!” 12 እነዚህ ሕዝቦች ግን የእግዚአብሔርን ዕቅድ አላወቁም፤ የሚወቃ የእህል ነዶ በአውድማ ላይ እንደሚሰበሰብ እግዚአብሔር እነርሱን ራሳቸውን የሰበሰባቸው ለቅጣት መሆኑን አልተገነዘቡም። 13 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ሂዱና ጠላቶቻችሁን እንደ እህል አበራዩ! ቀንዱ ብረት፥ ሰኮናው ነሐስ እንደ ሆነ በሬ ብርቱ አደርጋችኋለሁ፤ ብዙ መንግሥታትን ትደመስሳላችሁ፤ እነርሱ በግፍ የሰበሰቡትን ሀብትና ንብረት ሁሉ ለመላው ዓለም ጌታ ለእኔ ለእግዚአብሔር አምጥታችሁ ታቀርባላችሁ።” |