Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዳንኤል 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “ሜዶናዊው ዳርዮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ እርሱን ለማገዝና ለማበረታታት በአጠገቡ ቆሜ ነበር።

2 እኔም አሁን የምነግርህ ነገር እውነት ነው።” ያም ሰው የሚመስለው መልአክ እንዲህ ሲል ንግግሩን ቀጠለ፦ “ሌሎች ሦስት ነገሥታት በፋርስ ላይ ይነግሣሉ፤ ከእነርሱ የሚከተለው አራተኛው ንጉሥ ከሌሎቹ ይልቅ በሀብት የከበረ ይሆናል፥ ከሀብቱም የተነሣ ኀይሉ በበረታ ጊዜ ሌሎቹን መንግሥታት በማስተባበር በግሪክ መንግሥት ላይ ይነሣል።


የግብጽና የአሦር መንግሥታት አነሣሥ

3 “ከዚያን በኋላ ጦረኛ የሆነ አንድ ብርቱ ንጉሥ ይነሣል፤ የመንግሥቱ ግዛት ታላቅ ይሆናል፤ የፈለገውንም ሁሉ ያደርጋል።

4 ነገር ግን ኀይሉ በገነነ ጊዜ መንግሥቱ ይፈርስና በአራት የዓለም ማእዘን ይከፈላል፤ በቦታውም የእርሱ ዘሮች ያልሆኑ ነገሥታት ይተካሉ፤ ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዱ እንኳ የእርሱን ያኽል ኀይል አይኖረውም፤ ይህም የሚሆነው ያ መንግሥት ፈርሶ እንደገና ለሌሎችም ስለሚከፋፈል ነው።

5 “የደቡብ ንጉሥ ማለትም የግብጽ ንጉሥ እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ከጦር አዛዦቹ አንዱ ከእርሱ ይልቅ የበረታ ሆኖ እጅግ ታላቅ ለሆነ መንግሥት መሪ ይሆናል።

6 ከጥቂት ዓመቶች በኋላ የግብጽ ንጉሥ ከሶርያ ንጉሥ ጋር የወዳጅነት ቃል ኪዳን ይመሠርታል፤ ሴት ልጁንም ለሶርያ ንጉሥ ይድርለታል፤ ነገር ግን እርስዋ ኀይልዋን ለማጠናከር ካለመቻልዋ የተነሣ የንጉሡ ኀይል ስለማይጸና የወዳጅነቱም ውል ጸንቶ አይኖርም፤ ስለዚህም እርስዋ ከደጋፊዎችዋ፥ ከልጆችዋና ከአገልጋዮችዋ ጋር ትገደላለች።

7 ወዲያውኑ የእርስዋ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ይነግሣል፤ ከሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ጋር ጦርነት ይገጥማል፤ ምሽጋቸውንም ሰብሮ በመግባት ድል ይነሣቸዋል።

8 የአማልክታቸውንም ምስሎች ከወርቅና ከብር ዕቃዎች ጋር ማርኮ ወደ ግብጽ ይወስዳል፤ ለጥቂት ዓመቶችም የግብጹ ንጉሥ የሶርያን ንጉሥ በጦርነት ለማጥቃት አይነሣም።

9 ከዚያ በኋላ የሶርያ ንጉሥ የግብጽን ንጉሥ ግዛት ለመውረር ይመጣል፤ ነገር ግን በመጣበት እግሩ ወደ አገሩ እንዲመለስ ይገደዳል።

10 “የሶርያ ንጉሥ ወንዶች ልጆች ለጦርነት በመዘጋጀት ታላቅ ሠራዊት ያደራጃሉ፤ ከእነርሱ አንዱ ጠራርጎ እንደሚወስድ እንደ ኀይለኛ ጐርፍ ሆኖ በማለፍ በጠላት ምሽግ ላይ አደጋ ይጥላል።

11 በዚያን ጊዜ የግብጽ ንጉሥ እጅግ ተቈጥቶ የሶርያን ንጉሥ ለመውጋት ይነሣሉ፤ የሶርያ ንጉሥ ያሰለፈውንም ታላቅ ሠራዊት ያሸንፋል።

12 ብዙ ተዋጊዎችን ስለሚማርክ ልቡ ይታበያል፤ ከዚያም በብዙ ሺህ የሚቈጠሩትን ይፈጃል፤ ይሁን እንጂ በድል አድራጊነቱ ጸንቶ አይኖርም።

13 “የሶርያም ንጉሥ ወደ አገሩ ተመልሶ ከበፊቱ የበለጠ የጦር ሠራዊት ያደራጃል፤ ከጥቂት ዓመቶችም በኋላ ሠራዊቱን ከተሟላ ትጥቅ ጋር አሰልፎ ይመጣል።

14 ከዚያ በኋላ ብዙ ሰዎች በግብጽ ንጉሥ ላይ ያምፃሉ፤ ዳንኤል ሆይ! በዚህ ራእይ የታየው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ከአንተም ወገኖች አንዳንድ የዐመፅ ሰዎች ሁከት ያስነሣሉ፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም።

15 ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ በአንዲት በተመሸገች ከተማ ላይ ከበባ አድርጎ ይይዛታል፤ የግብጽም ወታደሮች እርሱን መቋቋም ይሳናቸዋል፤ ከእነርሱ ምርጥ የሆኑት እንኳ እርሱን ለመቋቋም በቂ ኀይል አይኖራቸውም።

16 ከወደ ሰሜን የሚመጣው ወራሪ የፈለገውን ያደርጋል፤ እርሱን ቆሞ የሚመክት አይኖርም፤ እርሱ የተቀደሰችውን አገር እንኳ ሳይቀር ወሮ ይይዛታል።

17 “የሶርያ ንጉሥ መላ ሠራዊቱን ሰብስቦ ለመዝመት ያቅዳል፤ የጠላትን መንግሥት ለመደምሰስ ሴት ልጁን በመዳር ከጠላት ንጉሥ ጋር የትብብር ስምምነት ይዋዋላል፤ ይሁን እንጂ ዕቅዱ አይሳካለትም።

18 ከዚያ በኋላ በባሕር ጠረፍ ባሉት አገሮች ላይ አደጋ ጥሎ ከእነርሱ ብዙዎቹን ይይዛል፤ ነገር ግን አንድ የጦር መሪ ድል ስለሚነሣው የትዕቢቱ ፍጻሜ ይሆናል፤ በእርግጥም በትዕቢት የተናገረው ስድብ ሁሉ በእርሱ ላይ ይፈጸማል።

19 ከዚያ በኋላ ንጉሡ ወደ ገዛ አገሩ ምሽጎች ይመለሳል፤ ነገር ግን ተሰናክሎ ስለሚወድቅ ዳግመኛ አይታይም።

20 “ሌላም ንጉሥ በእርሱ ቦታ ይተካል፤ ይህ ንጉሥ የመንግሥቱን ክብር ለመጠበቅ አንድ ግብር አስገባሪ ይሾማል፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያ ንጉሥ ይገደላል፤ ቢሆንም የሚገደለው በሕዝብ ዐመፅ ወይም በጦርነት አይደለም።”


ጨካኙ የሶርያ ንጉሥ

21 ራእዩን ያብራራልኝ የነበረውም መልአክ እንዲህ አለ፦ “ከእርሱ በኋላ አንድ የተናቀ ሰው ይነሣል፤ የንጉሥነት ክብር ግን አልተሰጠውም፤ ነገር ግን በድንገት መጥቶ በተንኰል የመንግሥቱን ሥልጣን ይይዛል።

22 የእግዚአብሔር ሊቀ ካህናት ሳይቀር እርሱን የሚቃወም ሠራዊት ሁሉ ከፊቱ ተጠራርጎ ይጠፋል።

23 በተንኰል የሰላም ውል በመደራደር ሌሎችን ያታልላል፤ የእርሱ ተከታዮች ጥቂቶች ቢሆኑም እየበረታ ይሄዳል።

24 እጅግ ሀብታም የሆነ አንድ ክፍለ ሀገር በድንገት ይይዛል፤ ከቀድሞ አባቶቹ አንዱ እንኳ ያላደረገውን ነገር ሁሉ ያደርጋል፤ በጦርነት የማረከውንም ዕቃና ንብረት ሁሉ ለጭፍሮቹ ያከፋፍላል፤ በምሽጎች ላይ አደጋ ለመጣል ዕቅድ ያወጣል፤ ነገር ግን ለጥቂት ጊዜ ነው።

25 “ትልቅ የጦር ኀይል አደራጅቶ በድፍረት በግብጽ ንጉሥ ላይ ይዘምታል፤ የግብጽ ንጉሥም በበኩሉ እጅግ ታላቅ የሆነ የጦር ኀይል አዘጋጅቶ የመጣበትን ጦር ይመክታል፤ ነገር ግን የግብጹ ንጉሥ ሤራ ስለሚደረግበት አይሳካለትም።

26 አብረውት የሚመገቡ የቅርብ ወዳጆቹ ያጠፉታል። ሠራዊቱም ይደመሰሳል፤ ብዙዎችም በጦርነት ይሞታሉ።

27 ከዚያን በኋላ ሁለቱ ነገሥታት በልባቸው ተንኰል እንደ ያዙ አብረው ለመመገብ በአንድ ገበታ ይቀመጣሉ፤ አንዱ ሌላውን ለማታለል የሐሰት ቃላት ይለዋወጣሉ፤ ሆኖም የተወሰነው ጊዜ ገና ስለ ሆነ እንዳሰቡት አይከናወንላቸውም።

28 የሶርያ ንጉሥ የማረከውን ሀብት ሁሉ ይዞ ይመለሳል፤ ልቡ ግን የተቀደሰውን ቃል ኪዳን ለማጥፋት ነው፤ የፈለገውን ሁሉ ካደረገ በኋላ ወደ አገሩ ይሄዳል።

29 “ከተወሰነው ጊዜ በኋላ ግብጽን እንደገና ይወራል፤ ይሁን እንጂ እንደ በፊቱ አይሳካለትም።

30 ሮማውያን በመርከብ መጥተው ስለሚወጉት በብርቱ ይደነግጣል፤ ወደ ኋላውም አፈግፍጎ በታላቅ ቊጣ ለአይሁድ የተሰጠውን የተቀደሰ ቃል ኪዳን ያረክሳል፤ ተመልሶም ሃይማኖታቸውን ከካዱት ሰዎች ጋር ይወዳጃል።

31 ሠራዊቱም ቤተ መቅደሱንና አካባቢውን ያረክሳሉ፤ የዘወትር መሥዋዕትም እንዳይቀርብ ያደርጋሉ፤ አጸያፊ የሆነ ርኩስ ነገር በማቆም ጥፋትን ያመጣሉ።

32 ንጉሡ ቀደም ብለው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን የካዱትን ሁሉ በማታለል የእነርሱን ድጋፍ ያገኛል፤ እግዚአብሔርን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች ግን ይበረታሉ፤ ንጉሡንም አጥብቀው ይቃወሙታል።

33 በሕዝቡ መካከል ያሉ ጠቢባን ሕዝቡን በማስተማር ዕውቀት እንዲያገኝ ያደርጋሉ፤ ነገር ግን ለጥቂት ጊዜ ለእሳት ቃጠሎና ለሰይፍ ስለት የተጋለጡ ይሆናሉ፤ ሀብታቸውንም ተዘርፈው ይታሰራሉ።

34 ይህ ከባድ ችግር በወደቀባቸው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች መጠነኛ ርዳታ ያደርጉላቸዋል፤ ብዙዎች በታማኝነት ሳይሆን በአስመሳይነት ከእነርሱ ጋር ይተባበራሉ።

35 ከጠቢባን አንዳንዶቹ ከባድ መከራ ይደርስባቸዋል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ምክንያት ነጥረውና ጠርተው በመውጣት እንከን የሌለባቸው ይሆናሉ፤ ይህም ሁኔታ የሚዘልቀው እግዚአብሔር ያቀደው መጨረሻ ጊዜ እስከሚደርስ ነው።

36 “የሶርያ ንጉሥ የፈለገውን ሁሉ ይፈጽማል፤ ራሱንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ከአማልክት ሁሉ በላይ ባለው አምላክ ላይ ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማይታወቅ የስድብ ቃል ይናገራል፤ የታቀደው ሁሉ መደረግ ስላለበት የእግዚአብሔር የቊጣው ቀን እስኪደርስ ድረስ ይሳካለታል።

37 ንጉሡ የቀድሞ አባቶቹን አማልክት ያቃልላል፤ ሴቶች የሚወዱአቸውንም አማልክት ይንቃል፤ እርሱ ራሱን ከሁሉ በላይ አድርጎ ስለሚቈጥር አማልክትን ሁሉ ችላ ይላል።

38 ከነዚህ ይልቅ፥ ምሽጎችን የሚጠብቅ ባዕድ አምላክን ያከብራል፤ በቀድሞ አባቶቹ ላልታወቀ አምላክ ወርቅ፥ ብር፥ ጌጣጌጥ የከበሩ ድንጋዮችንና ሌሎችንም ውድ ስጦታዎች በማቅረብ ያከብራል።

39 ምሽጎቹን ይጠብቁለት ዘንድ ባዕድ አምላክን የሚያመልኩ ሰዎችን ይመድባል፤ መሪነቱን የሚያውቁለትን ሁሉ ታላቅ ክብር በመስጠት በሕዝብ ላይ ይሾማቸዋል፤ ለዋሉለትም ውለታ ርስት ያካፍላቸዋል።

40 “ጊዜው ሲደርስ የግብጽ ንጉሥ በሶርያ ንጉሥ ላይ አደጋ ይጥልበታል፤ ሆኖም የሶርያ ንጉሥ በሠረገሎች፥ በፈረሶችና በመርከቦች በመጠቀም በብርቱ ጦርነት ይቋቋመዋል፤ እንደ ጐርፍ ውሃ በመጠራረግ ብዙ አገሮችን ይወራል።

41 ውብ የሆነችውንም የተስፋይቱን ምድር ይወራል፤ ብዙ አገሮችም በእርሱ እጅ ይወድቃሉ፤ ነገር ግን የኤዶም፤ የሞአብና የዐሞን አገሮች ከወረራው ያመልጣሉ።

42 ሥልጣኑን በብዙ አገሮች ላይ በሚያንሰራፋበትም ጊዜ ግብጽም ራስዋ አታመልጥም።

43 የግብጽን ወርቅ፤ ብርና ሌላውንም የከበረ ነገር ሁሉ ከተደበቀበት ቦታ ይወስዳል፤ ሊቢያንና ኢትዮጵያንም ድል ያደርጋል፤

44 ከዚያን በኋላ ከምሥራቅና ከሰሜን የሚመጣው ወሬ ያስደነግጠዋል፤ በታላቅ ቊጣ ተነሣሥቶ ብዙ ሰዎችን በማጥፋት እንዳልነበሩ ያደርጋል።

45 በባሕሩና ቤተ መቅደሱ በተሠራበት ውብ ኮረብታ መካከል ባለው ስፍራ ታላላቅ ንጉሣዊ ድንኳኖችን ይተክላል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ በመጨረሻው ራሱ ይጠፋል፤ የሚረዳውም አያገኝም።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos