ኢሳይያስ 41:13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ‘አይዞህ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥ ቀኝ እጅህን ይዤ እረዳሃለሁ’ እያልኩ የማበረታታህ፥ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና አትፍራ ይልሃል፤ እረዳሃለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እኔ አምላክህ ጌታ ነኝ፦ “አትፍራ፥ እረዳሃለሁ” ብዬ ቀኝህን የያዝኩ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ቀኝ እጅህን የያዝሁህ፥ እንዲህም የምልህ እኔ አምላክህ ነኝና። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፦ አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና። |
ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ! ባላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር እናንተን ለማዳን የሚያደርገውን ዛሬ ታያላችሁ፤ እነዚህን ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም።
ሙሴም “አይዞአችሁ፥ አትፍሩ፤ እግዚአብሔር በዚህ ሁኔታ ወደ እናንተ የመጣው ሊፈትናችሁና እርሱን በመፍራት ኃጢአት ከመሥራት ርቃችሁ እንድትኖሩ ነው” ሲል መለሰላቸው።
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ! እኔ አምላክህ ነኝ፥ ተስፋ አትቊረጥ! እኔ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤ ድል ነሺ በሆነ ክንዴ እደግፍሃለሁ።
“ወንዶች ልጆቼ ከሩቅ አገር እንዲመጡ በሰሜን በኩል ያሉትን አገሮች ተዉአቸው፥ በደቡብ በኩል ያሉትን አገሮች ‘አትያዙአቸውም’ ብዬ አዛለሁ።
ሕዝቦች በሥልጣኑ ሥር እንዲገዙ ለማድረግ፥ ነገሥታትን ከሥልጣን እንዲያወርድ፥ የከተሞችን ቅጽር በሮች ይከፍትለት ዘንድ ቀኝ እጁን ለያዘውና ቀብቶ ላነገሠው ንጉሥ ቂሮስን እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል፦
የአገልጋዬ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ፥ አትፍሩ ተስፋም አትቊረጡ፤ ከሩቅ አገር በደኅና እመልሳችኋለሁ፤ ልጆቻችሁንም ተማርከው ከተወሰዱበት አገር እመልሳቸዋለሁ፤ እስራኤላውያን እንደገና ሰላም አግኝተው ያለ ስጋት ይኖራሉ።
“የአገልጋዬ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! አትፍሩ ተስፋም አትቊረጡ፤ እናንተን ከሩቅ አገር፥ ዘራችሁንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ። እናንተም እንደገና ማንም ሳያስፈራችሁ በሰላምና በደኅንነት ትኖራላችሁ።
ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ ‘እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ’ ብዬ በሰጠሁት የተስፋ ቃል መሠረት አሁንም መንፈሴ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነ አይዞአችሁ አትፍሩ” ብሎ ነገራቸው።