Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ኤርምያስ 46 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር በግብጽ ላይ የፈረደው ፍርድ

1-2 እግዚአብሔር ከግብጽ ጀምሮ ስለ መንግሥታት ሁሉ ተናገረኝ፤ ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ በአራተኛው ዓመት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በሚገኘው ካርከሚሽ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ነኮ ተብሎ የሚጠራው የግብጽ ንጉሥ ያዘመተውን ሠራዊት፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ድል ስለ ማድረጉ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፦

3 “ጋሻችሁን አዘጋጁ፤ ወደ ጦር ሜዳም ዝመቱ፤

4 ፈረሶቻችሁን ለጒማችሁ ርካብ ረግጣችሁ ውጡ፤ የራስ ቊር ደፍታችሁ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ጦራችሁን ወልውሉ፤ የጦር ልብሳችሁንም ልበሱ።

5 “ነገር ግን ይህ የማየው ነገር ምንድን ነው? ከፍርሃት የተነሣ ወደ ኋላ በመመለስ ላይ ናቸው፤ ወታደሮቻቸው ድል ሆኑ፤ በየአቅጣጫው ፍርሀትና ሽብር ስላለ ወደ ኋላ መለስ ብለው ሳያዩም ወደ ፊት ሸሹ።

6 ነገር ግን ፈጣኖች እንኳ ሸሽተው አያመልጡም፤ ጐበዞችም ራሳቸውን ማዳን አይችሉም፤ ከኤፍራጥስ በስተሰሜን በኩል ተሰናክለው ይወድቃሉ።

7 ይህ እንደ ዓባይ ወንዝ የሚነሣና ሞልቶ በጐርፉ ዳርቻውን ሁሉ እንደሚያጥለቀልቅ ወንዝ የሆነ ይህ ማን ነው?

8 እንደ ዓባይ ወንዝ የተነሣችውና ሞልቶ በጐርፉ ዳርቻውን ሁሉ እንደሚያጥለቀልቅ ወንዝ የሆነችው ግብጽ ነች፤ ግብጽ እንዲህ ብላለች ‘እኔ ተነሥቼ ዓለምን አጥለቀልቃለሁ። ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን ሕዝብ ሁሉ እደመስሳለሁ።’

9 ፈረሶች ወደ ፊት እንዲሄዱ፥ ሠረገሎችም አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት እንዲሽከረከሩ እዘዙ፤ ከኢትዮጵያና ከሊቢያ ጋሻቸውን አንግበው በመጡ ሰዎችና፥ ከልድያ በመጡ ቀስት በሚወረውሩ ኀያላን ሰዎች ጭምር የተጠናከሩ ወታደሮችን ላኩ” ይላል እግዚአብሔር።

10 ይህ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር የመረጠው ቀን ነው፤ እርሱ ዛሬ የበቀል እርምጃ ይወስዳል፤ ጠላቶቹንም ይቀጣል። የእርሱም ሰይፍ ብዙዎችን ይበላል፤ በደማቸውም ይለወሳል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ሰሜን የሚገኙ ምርኮኞቹን መሥዋዕት ያደርጋቸዋል።

11 እንደ ድንግል የምትታዪ ግብጽ ሆይ! ወደ ገለዓድ ሄደሽ የሚቀባ መድኃኒት ፈልጊ፤ የአንቺ መድኃኒት ሁሉ ከንቱ ነው፤ ሊፈውስሽ የሚችል ነገር ከቶ የለም።

12 ሕዝቦች ሁሉ ስለ ኀፍረትሽ ሰምተዋል፤ የዓለምም ሕዝብ ሁሉ ጩኸትሽን አድምጠዋል፤ አንዱ ወታደር ሌላውን ወታደር ሲያደናቅፈው ሁሉም ተያይዞ መሬት ይወድቃል።


የናቡከደነፆር አመጣጥ

13 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በግብጽ ላይ አደጋ ለመጣል ስለ መምጣቱ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥

14 “የግብጽ ከተሞች በሆኑት በሚግዶል፥ በሜምፊስ በጣፍናስ ይህን ቃል ዐውጅ፤ ‘ራሳችሁን ለመከላከል ተዘጋጁ፤ በዙሪያችሁ ያለው ሁሉ በጦርነት ይጠፋል።

15 ኀያል ነው የምትሉት አጲስ የተባለው ጣዖት ስለምን ወደቀ? እግዚአብሔር ገፍቶ ስለ ጣለው አይደለምን?’

16 ጀሌዎቻቸው ተሰናክለው አንዱ በአንዱ ላይ ይወድቃሉ፤ እርስ በርሱም አንዱ ሌላውን፥ ‘ከጠላት ሰይፍ አምልጠን ከሀገራችን ሕዝብ መቀላቀል እንድንችል እንፍጠን’ ይለዋል።”

17 የግብጽን ንጉሥ “በዕድሉ የማይጠቀም ለፍላፊ፥” በሚል አዲስ ስም ይጠሩታል፤

18 “ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ተብሎ የሚጠራው ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ “እኔ ሕያው ነኝ፤ በተራሮች መካከል ታቦር፥ በባሕር አጠገብ ቀርሜሎስ ከፍ ብለው እንደሚታዩ እንደዚሁ በእናንተ ላይ ከፍ ብሎ የሚታይ፥ ኀይል ይመጣል።

19 የግብጽ ሕዝብ ሆይ! ተማርካችሁ የምትሄዱ ስለ ሆነ ዕቃችሁን አዘጋጁ፤ ሜምፊስ ፈራርሳ ሰው የማይኖርባት በረሓ ትሆናለች፤

20 ግብጽ እንደ ተዋበች ጊደር ናት፤ እርስዋ ከሰሜን በኩል በመጣ ተናካሽ ዝንብ ትወረራለች።

21 ቅጥረኞች ወታደሮችዋም እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤ ወደ ኋላ ተመልሰው ይሸሻሉ፤ የፍርድና የጥፋት ቀን ስለ ደረሰባቸው፥ ጸንተው መዋጋት አይችሉም።

22-23 የጠላት ሠራዊት ኀይል ሲቃረብ ግብጽ እንደ እባብ የፉጨት ድምፅ እያሰማች ትሸሻለች፤ ሰዎች ጥቅጥቅ ያለውን ደን እንደሚመነጥሩ በመጥረቢያ አደጋ ይጥሉባታል። የሰዎቻቸው ብዛት በቊጥር አይደረስበትም፤ የወታደሮቻቸውም ብዛት ከአንበጣ ሠራዊት ይበልጣል፤

24 የግብጽ ሕዝብ በሰሜን ሕዝብ ስለሚሸነፉ ያፍራሉ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

25 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ግብጽን፥ አማልክትዋንና ነገሥታቶችዋን፥ የቴብስ አምላክ የሆነውን አሞንን፥ የግብጽን ንጉሥና በእርሱ የሚተማመኑትን ሁሉ እቀጣለሁ።

26 ሊገድሉአቸው ለሚፈልጉ ለባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ለሠራዊቱ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ሆኖም ዘግየት ብሎ ከዚህ በፊት እንደሆነው ሁሉ ግብጽ እንደገና የሰዎች መኖሪያ ትሆናለች፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”


እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚታደግ

27 “የአገልጋዬ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! አትፍሩ ተስፋም አትቊረጡ፤ እናንተን ከሩቅ አገር፥ ዘራችሁንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ። እናንተም እንደገና ማንም ሳያስፈራችሁ በሰላምና በደኅንነት ትኖራላችሁ።

28 እኔ ከእናንተ ጋራ ስለ ሆንኩ አገልጋዮቼ እስራኤላውያን ሆይ! እናንተ አትፍሩ፤ እናንተ በሀገራቸው እንድትበታተኑ ያደረግኹባቸውን ሕዝቦች ሁሉ አጠፋለሁ፤ እናንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋችሁም፤ ሆኖም ለማረም እቀጣችኋለሁ፤ ሳልቀጣችሁ ግን አላልፍም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos