Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ጢሞቴዎስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 በእግዚአብሔርና እንዲሁም መንግሥቱን በሚያቋቁምበት ጊዜ፥ በሕያዋንና በሙታን ላይ በሚፈርደው በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ዐደራ እልሃለሁ፤

2 ቃሉን ስበክ፤ ቢመችም ባይመችም በማንኛውም ጊዜ ተግተህ ሥራ፤ እያስረዳህ እየገሠጽክና እየመከርክ፥ በትዕግሥትና በማስተማር ትጋ።

3 ሰዎች ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት ለመስማት የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን ለወሬ በመጐምጀት እነርሱ ራሳቸው የሚወዱትን ነገር የሚነግሩአቸውን አስተማሪዎች ይሰበስባሉ።

4 ስለዚህ እውነትን መስማት ትተው ተረትን መስማት ይወዳሉ።

5 አንተ ግን በሁሉ ነገር ጥንቁቅ ሁን፤ መከራን በመቀበል ጽና፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አከናውን፤ አገልግሎትህንም ሁሉ ፈጽም።

6 እኔ ግን መሥዋዕት ለመሆን ተቃርቤአለሁ፤ ከዚህ ዓለም ተለይቼ የምሄድበት ጊዜም ደርሶአል፤

7 ጦርነትን በመልካም ተዋግቻለሁ፤ የእሽቅድድም ሩጫዬን እስከ መጨረሻው ሮጫለሁ፤ እምነትን ጠብቄአለሁ።

8 ከእንግዲህ ወዲህ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፤ ይህንንም አክሊል ያ ትክክለኛ ፍርድን ፈራጁ ጌታ በዚያን ቀን ይሰጠኛል፤ የሚሰጠውም ለእኔ ብቻ ሳይሆን የእርሱን መገለጥ ለሚወድዱ ሁሉ ነው።


ስለ ግል ጉዳዮች

9 በፍጥነት ወደ እኔ እንድትመጣ ይሁን፤

10 ዴማስ ይህን ዓለም ወዶ ተለይቶኛል፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል፤ ቄርቂስ ወደ ገላትያ፥ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል።

11 ከእኔ ጋር ያለው ሉቃስ ብቻ ነው፤ ማርቆስ ለአገልግሎት ስለሚጠቅመኝ ፈልገህ ይዘኸው ና።

12 ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ።

13 ስትመጣ በጢሮአዳ በካርፑስ ዘንድ የተውኩትን ካባ ይዘህልኝ ና፤ መጻሕፍቱንም ይልቁንም የብራና መጻሕፍቱን አምጣልኝ።

14 የናስ አንጥረኛው እስክንድር ከፍተኛ ጒዳት አደረሰብኝ፤ ጌታ እንደ ሥራው ይከፍለዋል።

15 እርሱ እኛ የምንናገረውን በብርቱ ስለሚቃወም አንተም ራስህ ከእርሱ ተጠንቀቅ።

16 በተከሰስኩበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ባቀረብኩ ጊዜ ሁሉም ተለዩኝ እንጂ ከእኔ ጋር ሆኖ የረዳኝ ማንም አልነበረም፤ ይህንንም ነገር እግዚአብሔር እንደ በደል አድርጎ አይቊጠርባቸው።

17 ነገር ግን መልእክቱ በእኔ አማካይነት በሙሉ እንዲነገርና አሕዛብ ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ ከእኔ ጋር ሆኖ አበረታኝ፤ ከአንበሳም አፍ ድኛለሁ።

18 ጌታ ከማንኛውም ክፉ ነገር ያድነኛል፤ በሰማይ ላለው መንግሥቱም ያበቃኛል፤ ለእርሱ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን! አሜን።


የመጨረሻ ሰላምታ

19 ለጵርስቅላና ለአቂላ፥ ለኦኔሲፎርም ቤተሰቦች ሰላምታ አቅርብልኝ።

20 ኤራስጦስ በቆሮንቶስ ቀርቶአል፤ ጥሮፊሞስ ስለ ታመመ በሚሊጢ ትቼዋለሁ።

21 ክረምት ሳይገባ ወደ እኔ እንድትመጣ ይሁን። ኤውቡሉስ፥ ጱዴስ፥ ሊኖስ፥ ቅላውዲያና አማኞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።

22 ጌታ ከአንተ ጋር ይሁን። የእግዚአብሔር ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos