Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 118 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ ድል አድራጊነት የቀረበ የምስጋና ጸሎት

1 ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ።

2 የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ።

3 የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑት የአሮን ልጆች ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ።

4 የሚፈሩት ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ።

5 በተጨነቅሁ ጊዜ ጩኸቴን ወደ እግዚአብሔር አሰማሁ፤ እርሱም ሰማኝ፤ ነጻም አወጣኝ።

6 እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚረዳኝ አልፈራም፤ ከቶ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?

7 እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚረዳኝ፥ የጠላቶቼን ውድቀት አያለሁ።

8 በሰው ከመመካት ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።

9 በመሪዎች ከመመካት ይልቅ፥ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።

10 ብዙ ሕዝቦች ከበውኝ ነበር፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ደመሰስኳቸው።

11 ከየአቅጣጫው በዙሪያዬ ነበሩ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ደመሰስኳቸው።

12 ዙሪያዬን እንደ ንብ ከበቡኝ፤ ነገር ግን እሾኽ በእሳት እንደሚቃጠል በፍጥነት ተቃጠሉ፤ በእግዚአብሔርም ኀይል ደመሰስኳቸው።

13 ብርቱ ጥቃት ደርሶብኝ፥ ለመውደቅ ተቃርቤ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ረዳኝ።

14 እግዚአብሔር ከለላዬና መከላከያዬ ነው፤ አዳኜም እርሱ ነው።

15 በጻድቃን ድንኳን ውስጥ እንዲህ የሚል የድል አድራጊነት ድምፅ ይሰማል፦ “የእግዚአብሔር ኀይል ያሸንፋል!”

16 የእግዚአብሔር ኀይል ከፍ ከፍ አለ፤ ኀይሉም ድል አድራጊ ነው።

17 በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤ የእግዚአብሔርንም ድንቅ ሥራ ዐውጃለሁ።

18 በብርቱ ቀጥቶኛል፤ ነገር ግን እንድሞት አላደረገኝም።

19 ወደ ውስጥ ገብቼ እግዚአብሔርን እንዳመሰግን የቤተ መቅደስን በሮች ከፈቱልኝ።

20 ይህ የእግዚአብሔር በር ነው፤ ጻድቃን በእርሱ ይገባሉ።

21 እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ሰማኸኝና ስላዳንከኝ አመሰግንሃለሁ።

22 ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ ዋና የማእዘን ራስ ሆነ።

23 ይህም የእግዚአብሔር ሥራ ነው፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው።

24 ይህ እግዚአብሔር የሠራው የድል ቀን ነው፤ በእርሱ ደስ ይበለን፤ ሐሴትም እናድርግ!

25 እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ አድነን! እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ ሁሉ ነገር የተሟላ እንዲሆን አድርግልን!

26 በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ይሁን! በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆነን እንባርካችኋለን።

27 እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ ብርሃንን ሰጥቶናል፤ ለምለም የሆኑ ቅርንጫፎችን ይዘን በዓል ለማክበር ወደ መሠዊያው እንሂድ።

28 አንተ አምላኬ ስለ ሆንክ አመሰግንሃለሁ፤ ታላቅነትህንም ዐውጃለሁ።

29 ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos