ኤፌሶን 6:5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንተ አገልጋዮች ሆይ! በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ታዘዙ፤ ለክርስቶስ በምታገለግሉት ዐይነት በልብ ቅንነት ታዘዙአቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ባሮች ሆይ፤ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ፣ በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑት በአክብሮትና በፍርሀት፣ በቅን ልብም ታዘዙ፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አገልጋዮች ሆይ! ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ፥ በልባችሁ ቅንነት በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አገልጋዮችም በሥጋችሁ ለሚገዙአችሁ ጌቶቻችሁ በፍርሀትና በመደንገጥ፥ በሰፊ ልብም ለክርስቶስ እንደምትገዙ ታዘዙ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ |
አንተ የሰውን ሁሉ ልብ ፈትነህ፥ ታማኝ በሆነ ሕዝብ እንደምትደሰት ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም እኔ ይህን ሁሉ በፈቃዴ ለአንተ የሰጠሁት፥ በታማኝነትና በቅንነት ነው፤ ደግሞም እዚህ የተሰበሰበው ሕዝብህ ለአንተ ስጦታ በማቅረቡ፥ እጅግ መደሰቱን ተገንዝቤአለሁ፤
እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! አገልጋዮችና ገረዶች የአሳዳሪዎቻቸውን እጅ እንደሚጠባበቁ ሁሉ እኛም እስክትምረን ድረስ የአንተን ምሕረት ለማግኘት እንጠባበቃለን።
የሠራዊት አምላክ ካህናቱን እንዲህ ይላቸዋል፦ “ልጅ አባቱን፥ አገልጋይም አሳዳሪ ጌታውን ያከብራል፤ እነሆ፥ እኔ አባታችሁ ከሆንኩ ለምን አታከብሩኝም? ጌታችሁም ከሆንኩ ለምን ክብር አትሰጡኝም? እናንተ የእኔን ስም ንቃችኋል፤ ነገር ግን ‘ስምህን የናቅነው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ።
“አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ ወይም አንዱን ይጠላል፥ ሌላውንም ይወዳል፤ ወይም አንዱን ያከብራል፥ ሌላውን ይንቃል፤ እንዲሁም አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ አገልጋይ መሆን አይችልም።
እኔ ራሴ ለባለ ሥልጣኖች ታዛዥ ስሆን፥ ከእኔ በታች የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።”
የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም።
ሁላችሁም ታዛዦች እንደ ሆናችሁና በፍርሃትና በመንቀጥቀጥም እንደ ተቀበላችሁት ቲቶ ሲያስታውስ፥ ለእናንተ ያለው ፍቅር በጣም ታላቅ ሆኖአል።
ወዳጆቼ ሆይ! እኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ሁልጊዜ ታዛዦች እንደ ነበራችሁ፥ ይልቁንም አሁን ከእናንተ በራቅሁበት ጊዜ ይበልጥ ታዛዦች እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ፤ ስለዚህ እያንዳንዳችሁ መዳናችሁን ፍጹም ለማድረግ በፍርሃትና በአክብሮት ተግታችሁ ሥሩ።
ከእንግዲህ ወዲህ ከአንተ ጋር የሚኖረውም እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ የበለጠ ሆኖ እንደ ውድ ወንድም ነው፤ እርሱ ለእኔ ውድ ወንድም ነው፤ ይሁን እንጂ በሥጋ እርሱ በአገልግሎቱ ስለሚጠቅምህ በመንፈሱ ደግሞ በክርስቶስ ወንድምህ ስለ ሆነ ለአንተ ይበልጥ ተወዳጅ ነው።
ኢያሱ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት አገልግሉት፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶና በግብጽ ይሰግዱላቸው የነበሩትን ባዕዳን አማልክት አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ፤