ፊልሞና 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ ከሆንኩ ከእኔ ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፥ ለተወደደው ወንድማችንና የሥራ ጓደኛችን ለሆነው ለፊልሞና፥ 2 ለእኅታችን ለአፍብያ፥ ከእኛ ጋር የክርስቶስ ወታደር ለሆነው ለአርኪጳስ፥ እንዲሁም በቤትህ ለሚሰበሰቡ ምእመናን። 3 ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። የፊልሞና ፍቅርና እምነት 4 በጸሎቴ አንተን እያሰብኩ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ 5 በጌታ በኢየሱስ ያለህን እምነትና ለምእመናንም ያለህን ፍቅር ሰምቼአለሁ፤ 6 የክርስቶስ በመሆናችን ያለን መልካም ነገር ሁሉ በይፋ ይታወቅ ዘንድ እምነትህን ለሌሎች ለማካፈል እንድትተጋ እጸልያለሁ። 7 ወንድሜ ሆይ! በአንተ ምክንያት የምእመናን ልብ ስለ ታደሰ ፍቅርህ ታላቅ ደስታንና መጽናናትን ሰጥቶኛል። ጳውሎስ ስለ ኦኔሲሞስ ያቀረበው ምልጃ 8 ስለዚህ ተግባርህን ፈጽም ብዬ አንተን ለማዘዝ በክርስቶስ ድፍረት ነበረኝ፤ 9 ሆኖም እንደዚያ ከማድረግ ይልቅ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንኩት እኔ ሽማግሌው ጳውሎስ በፍቅር መለመንን እመርጣለሁ። 10 እኔ እስር ቤት እያለሁ ልጄ ስለ ሆነው ስለ ኦኔሲሞስ አንተን እለምንሃለሁ። 11 አናሲሞስ ከዚህ በፊት አይጠቅምህም ነበር፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ ጠቃሚ ነው። 12 እነሆ እርሱን ወደ አንተ መልሼ ልኬዋለሁ፤ እርሱን ወደ አንተ ስልከውም የገዛ ራሴን ልብ እንደ ላክሁ አድርጌ እቈጥረዋለሁ። 13 በወንጌል ምክንያት እዚህ ታስሬ ሳለሁ በአንተ ምትክ ሆኖ እንዲያገለግለኝ እርሱ ከእኔ ጋር ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር፤ 14 ነገር ግን የአንተ መልካም ሥራ በግዴታ ሳይሆን በውዴታ እንዲሆን ብዬ አንተን ሳላስፈቅድ ምንም ማድረግ አልፈለግሁም። 15 ኦኔሲሞስ እስከ አሁን ለጥቂት ጊዜ የተለየህ ምናልባት ከእንግዲህ ወዲህ ለሁልጊዜ ከአንተ ጋር እንዲኖር ይሆናል። 16 ከእንግዲህ ወዲህ ከአንተ ጋር የሚኖረውም እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ የበለጠ ሆኖ እንደ ውድ ወንድም ነው፤ እርሱ ለእኔ ውድ ወንድም ነው፤ ይሁን እንጂ በሥጋ እርሱ በአገልግሎቱ ስለሚጠቅምህ በመንፈሱ ደግሞ በክርስቶስ ወንድምህ ስለ ሆነ ለአንተ ይበልጥ ተወዳጅ ነው። 17 እንግዲህ እኔን እንደ ወንድም አድርገህ ከቈጠርከኝ ልክ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። 18 ያደረሰብህ በደል ቢኖር ወይም ዕዳ ቢኖርበት ዕዳውን በእኔ ላይ አድርገው። 19 እነሆ እኔ ጳውሎስ “ዕዳውን እከፍልሃለሁ” ብዬ በገዛ እጄ ጽፌ አረጋግጥልሃለሁ፤ ሆኖም ስለ ሕይወትህ አንተ ራስህ እንኳ የእኔ ባለዕዳ መሆንክን እኔ ላስታውስህ አያስፈልግም። 20 እንግዲህ ወንድሜ ሆይ! ይህን መልካም ነገር እንድታደርግልኝ በጌታ እለምንሃለሁ፤ እባክህ ልቤን በክርስቶስ አድስልኝ። 21 ይህን የጻፍኩልህ እንደምትታዘዘኝ በመተማመን ነው፤ እንዲያውም እኔ ከምጠይቅህ በላይ እንደምታደርግ ዐውቃለሁ። 22 በዚያውም እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ሰምቶ ወደ እናንተ እንድመጣ እንደሚያደርገኝ ተስፋ ስላለኝ የማርፍበትን ቤት አዘጋጅልኝ። የመጨረሻ ሰላምታ 23 በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ከእኔ ጋር የታሰረው ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብልሃል፤ 24 እንዲሁም የሥራ ጓደኞቼ የሆኑት ማርቆስ፥ አርስጥሮኮስ፥ ዴማስና፥ ሉቃስ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። 25 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። |