ዘካርያስ 8:13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ በረከት መሆን እንድትችሉ አድናችኋለሁ፤ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአሕዛብ መካከል የርግማን ምሳሌ ነበራችሁ፤ አሁን ግን አድናችኋለሁ፤ እናንተም በረከት ትሆናላችሁ። አትፍሩ፤ ነገር ግን እጃችሁን አበርቱ።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በሕዝቦች ዘንድ እንደ ርግማን ትቈጠሩ የነበራችሁት እናንተ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች ሆይ! እኔ አድናችኋለሁ፤ ለበረከትም ትሆናላችሁ፤ ስለዚህ አትፍሩ! በርቱ።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፣ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፥ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ። |
በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆናሉ፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤና ለክፉ ነገር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ባድማና መሣቀቂያ ማፍዋጫም እርግማንም ላደርጋቸው፥ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ነገሥታትዋንም አለቆችዋንም አጠጣኋቸው።
በሰይፍም በራብም በቸነፈርም አሳዳድዳቸዋለሁ፤ ባሳደድኋቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል ለመረገሚያና ለመሣቀቂያ ለማፍዋጫም ለመሰደቢያም ይሆናሉ፤ በምድር መንግሥታትም ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
“ይህ ሕዝብ፦ ‘ጌታ የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል’ ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ ባለመሆኑ ሕዝቤን አቃልለዋል።
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ተናግሮአልና፦ ቁጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ወረደ፥ እንዲሁ ወደ ግብጽ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይወርድባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለመሣቀቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ትሆናላችሁ፥ ይህንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩትም።
ወደ ግብጽም ለመግባት በዚያም ለመቀመጥ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ትሩፍ እወስዳለሁ፥ ሁሉም ይጠፋሉ፥ በግብጽም ምድር ይወድቃሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለመሣቀቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ።
ጌታም ከእንግዲህ ወዲህ የሥራችሁን ክፋትና ያደረጋችሁትን ርኩሰት መታገሥ አልቻለም፤ ስለዚህ ምድራችሁ ባድማ መሣቀቂያም መረገሚያም ሆናለች ዛሬም እንደሆነ የሚኖርባት የለም።
ሳምኬት። እናንተ ርኩሳን፥ ራቁ፥ ርቃችሁም ሂዱ፥ አትንኩ ብለው ጮኹባቸው። በሸሹና በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል፦ በዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም ተባለ።
እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እነሆ፦ “አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል፤ ፈጽመን ተቆርጠናል” ይላሉ።
በአንቺ ላይ በንዴትና በቁጣ፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ፥ በዙሪያሽ ላሉ አገሮች መሰደቢያና መተረቻ፥ ማስጠንቀቂያና ድንጋጤ ትሆኛለሽ፥ እኔ ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ።
በዱር አራዊት መካከል እንዳለ አንበሳ፥ በበጎች መንጋ መካከል አልፎ እንደሚረግጥ፥ የሚታደግም ሳይኖር እንደሚነጥቅ እንደ አንበሳ ደቦል፥ የያዕቆብ ትሩፍም በአሕዛብና በብዙ ሕዝቦች መካከል እንዲሁ ይሆናል።
በዚያ ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ በሰበሰብኳችሁም ጊዜ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ።
የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናንት፥ መቅደሱ እንዲሠራ የሠራዊት ጌታ ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ፥ እጃችሁን አበርቱ።
ይሁዳን እንደ ደጋኔ አጥፌዋለሁ፥ ኤፍሬምንም ቀስቱን አድርጌ አዘጋጅቻለሁ፤ ጽዮን ሆይ፥ ልጆችሽን በግሪክ ልጆች ላይ አስነሣለሁ፥ እንደ ተዋጊ ሰይፍም አደርግሻለሁ።
ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋናና በስም፥ በክብር ከፍ እንደሚያደርግህና እርሱም እንደ ተናገረ ለጌታ እግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ አደረገህ።”