Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በኢየሩሳሌም ላይ የመጣ ሰይፍ

1 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የተሳለ ሰይፍ ውሰድ፥ እንደ ጢም መላጫ ለራስህ ትወስደዋለህ፥ በራስህና በጢምህም አሳልፈው፥ ሚዛንንም ውሰድ ጠጉሩንም ትከፋፍለዋለህ።

2 የመከበብም ወራት ሲፈጸም አንድ ሦስተኛውን በከተማይቱ መካከል በእሳት ታቃጥለዋለህ፥ አንድ ሦስተኛውን ወስደህ ዙሪያውን በሰይፍ ትመታዋለህ፥ አንድ ሦስተኛውን ወደ ነፋስ ትበትነዋለህ፥ እኔም ከኋላቸው ሰይፍ እመዝዛለሁ።

3 ከዚህም ጥቂት ውሰድ፥ በመጐናጸፊያህም ቋጥራቸው።

4 ከእነዚህም እንደገና ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላቸዋለህ፥ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፥ ከእርሱም እሳት ወደ እስራኤል ቤት ሁሉ ትወጣለች።

5 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አገሮች በዙሪያዋ ሆነው፥ በመንግሥታት መካከል የተከልዃት ኢየሩሳሌም ይህች ናት።

6 እርሷም ከሕዝቦች ይልቅ በትእዛዛቴ ላይ፥ በዙሪያዋ ካሉ አገሮችም ሁሉ ይልቅ በሕጌ ላይ በክፋቷ አምፃለች፥ እነርሱ ትእዛዛቴን አንቀበልም ብለዋልና፥ በሕጌም አልኖሩምና።

7 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁካታችሁ በዙሪያችሁ ካሉት አገሮች ይልቅ ሆኗል፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንዳሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና

8 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፥ አገሮችም እያዩ በመካከልሽ ፍርድን አመጣብሻለሁ።

9 ስለ ርኩሰትሽ ሁሉ እስከ አሁን ያላደረግኹትን፥ ከዚህ በኋላም እርሱን የሚመስል የማላደርገውን ነገር በአንቺ ላይ አደርግብሻለሁ።

10 ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ፥ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፥ ፍርድንም አደርግብሻለሁ፥ ከአንቺም የተረፉትንም ሁሉ ወደ ሁሉም ነፋሳት እበትናለሁ።

11 ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር በእድፍሽ ሁሉና በርኩሰትሽም ሁሉ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ እኔም አሳንስሻለሁ፥ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም።

12 ከአንቺም አንድ ሦስተኛው በቸነፈር ይሞታሉ፥ በመካከልሽም በራብ ያልቃሉ፥ አንድ ሦስተኛውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ አንድ ሦስተኛውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ፥ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።

13 ንዴቴ ያልፋል፥ ቁጣዬም በእነርሱ ላይ እንዲያርፍ አደርጋለሁ፥ እጽናናለሁም፥ ቁጣዬን በእነርሱ ላይ በፈጸምሁ ጊዜ እኔ ጌታ በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ።

14 በዙሪያሽም ባሉ አገሮች መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ባድማና መሰደቢያ አደርግሻለሁ።

15 በአንቺ ላይ በንዴትና በቁጣ፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ፥ በዙሪያሽ ላሉ አገሮች መሰደቢያና መተረቻ፥ ማስጠንቀቂያና ድንጋጤ ትሆኛለሽ፥ እኔ ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ።

16 የሚገድሉና የሚያጠፉ የራብ ፍላፃ በወረወርሁ ጊዜ፥ እንዳጠፋችሁ እወረውራቸዋለሁ፥ በእናንተ ላይ ረሃብን እጨምርባችኋለሁ፥ የምግባችሁንም በትር እሰብራለሁ።

17 ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድባችኋለሁ፥ ልጆችሽን ያሳጡሻል፥ ቸነፈርና ደምም በአንቺ በኩል ያልፋሉ፥ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ። እኔ ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos