ኢሳይያስ 17:8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በእጃቸውም ወደ ሠሯቸው መሠዊያዎች አይመለከቱም፤ በጣቶቻቸው ወዳበጇቸው የዕጣን መሠዊያዎች ወይም ወደ ማምለኪያ ዐምዶች አይመለከቱም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በእጃቸውም ወደ ሠሯቸው መሠዊያዎች አይመለከቱም፤ በጣቶቻቸው ላበጇቸው የዕጣን መሠዊያዎች፣ ለአሼራም የአምልኮ ዐምዶች ክብር አይሰጡም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚያን በኋላ በገዛ እጃቸው በሠሩት መሠዊያ መታመናቸው ይቀራል፤ እንዲሁም የእጃቸው ሥራ በሆኑት በአሼራ ምስልና ዕጣን ሊያጥኑባቸው በሠሩአቸው መሠዊያዎች መተማመናቸውን ይተዋሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በጣዖታቸውና ጣቶቻቸው በሠሩአቸው የእጃቸው ሥራዎች አይተማመኑም፤ ለርኵሰታቸውም ዛፎችን አይቈርጡም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እጁም የሠራችውን መሠዊያ አይመለከትም፥ ጣቶቹም ወደ አበጁአቸው፥ ወደ ማምለኪያ ዐፀዶች ወይም ወደ ፀሐይ ምስሎች፥ አያይም። |
ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በዚያ የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው ሁሉንም ፈጽመው እስከሚያጠፏቸው ድረስ ሐውልቶቹን ሰባበሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጡ፥ በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኮረብታው መስገጃዎችና መሠዊያዎች አፈረሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ።
የበኣሊምንም መሠዊያዎች በእርሱ ፊት አፈረሱ፤ በእነርሱም ላይ የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎቹን የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረፁትንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሰባበረ፥ አደቀቃቸውም፥ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው።
በዚያን ቀን ከእስራኤል ዘር የተረፉት፤ ከያዕቆብም ቤት የዳኑት፤ ከእንግዲህ ወዲህ በመታቸው ላይ አይታመኑም፤ ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በጌታ ላይ፤ በእውነት ይታመናሉ።
በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ምክንያት የአሞራውያንና የኤዊያውያን ከተሞች ምድረ በዳ እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ጠንካራ ከተሞችህ ባድማም ይሆናሉ።
ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፥ ይህም ኃጢአትን የማስወገድ ፍሬ ነው።
በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን፥ በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፤ እንደ ርኩስም ነገር ትጥላቸዋለህ፦ “ከእኔ ራቁ!” ትላቸዋለህ።
ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፤ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል።
ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ እንደ አትክልት ስፍራ ይለመልማሉ፤ እንደ ወይንም ተክል ያብባሉ፤ መዓዛቸውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል።
ኤፍሬም ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ከጣዖታት ጋር እኔ ምን አደርጋለሁ? እኔ እመልስለታለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል።
ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሦች አጠፋለሁ፥ ክፉዎች እንዲደናቀፉ አደርጋለሁ፥ ሰውንም ከምድር ገጽ እቆርጣለሁ ይላል ጌታ።
በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ።
ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም አድቅቁት፥ የእነርሱንም አሼራ ሰባብሩ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ።