Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ዜና መዋዕል 34 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ኢዮስያስ መንገሡ

1 ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ።

2 በጌታም ፊት ቅን ነገር አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም።

3 በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመር፤ በዓሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታው መስገጃዎችና ከማምለኪያ ዐፀዶቹ፥ ከተቀረፁትና ቀልጠው ከተሰሩት ምስሎች ያነጻ ጀመር።

4 የበኣሊምንም መሠዊያዎች በእርሱ ፊት አፈረሱ፤ በእነርሱም ላይ የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎቹን የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረፁትንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሰባበረ፥ አደቀቃቸውም፥ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው።

5 የካህናቶቻቸውንም አጥንት በመሠዊያቸው ላይ አቃጠለ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ።

6 የምናሴንና የኤፍሬምንም የስምዖንና የንፍታሌምንም ከተሞች፥ በዙሪያቸውም ያለውን ቦታ እንዲሁ አነጻ።

7 መሠዊያዎቹንም አፈረሰ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንና የተቀረፁትን ምስሎች አደቀቀ፥ በእስራኤልም አገር ሁሉ የዕጣን መሠዊያዎቹን ሁሉ ቈራረጠ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።


የሕጉ መጽሐፍ መገኘቱ

8 በነገሠም በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የጌታን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የጌታን የአምላኩን ቤት እንዲጠግኑ ላካቸው።

9 ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም የደጆቹም ጠባቂዎች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ ጌታ ቤት ያመጡትን ገንዘብ ሰጡት።

10 የጌታንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ በጌታም ቤት የሚሠሩት ሠራተኞች ቤቱን ለሚጠግኑና ለሚያድሱ ሠራተኞች ሰጡ።

11 እነርሱም የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች እንዲሠሩ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ እንዲገዙ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ።

12 ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ

13 በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹም የደጁም ጠባቂዎች ከሌዋውያን ወገን ነበሩ።

14 ወደ ጌታም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የጌታን የሕግ መጽሐፍ አገኘ።

15 ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን፦ “የሕጉን መጽሐፍ በጌታ ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው።

16 ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም እንዲህ ብሎ አወራለት፦ “ባርያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ እያደረጉ ነው፤

17 በጌታም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፥ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ።”

18 ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ፦ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው።

19 ንጉሡም የሕጉን ቃላት በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።

20 ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦

21 “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለማድረግ አባቶቻችን የጌታን ቃል ስላልጠበቁ፥ በእኛ ላይ የነደደው የጌታ ቁጣ እጅግ ታላቅ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት ጌታን ጠይቁ።”


ነቢይቱ ሕልዳና ምክር እንድትሰጥ መጠየቅዋ

22 ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ የላካቸው ሰዎች ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርሷም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንንም ነገር ነገሩአት።

23 እርሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦

24 ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ አመጣለሁ።

25 በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቁጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።

26 ጌታን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃላት፥

27 ልብህ ተጸጽቶአልና፥ በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ የተናገርሁትን ቃላቴን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፥ ይላል ጌታ።

28 እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩባትም ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።


ቃል ኪዳኑ መታደሱ

29 ንጉሡም ላከ፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰበ።

30 ንጉሡም፥ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀመሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ ጌታ ቤት ወጡ፤ በጌታም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ እየሰሙት አነበበ።

31 ንጉሡም በስፍራው ቆሞ ጌታን ተከትሎ እንዲሄድ፥ ትእዛዛቱንና ምስክሩን ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በጌታ ፊት ቃል ኪዳን አደረገ።

32 በኢየሩሳሌምና በብንያምም የተገኙትን ሁሉ በዚህ ነገር አማለ፤ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት የአባቶቻቸው አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንደሚያዝዘው አደረጉ።

33 ኢዮስያስም ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩስ የሆነውን ነገር ሁሉ አስወገደ፥ በእስራኤልም የተገኙትን ሁሉ አምላካቸውን ጌታን እንዲያመልኩ አደረገ። በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ከመከተል አልራቁም።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos