2 ዜና መዋዕል 31 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የአሕዛብ መቅደሶች መፍረሳቸው 1 ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በዚያ የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው ሁሉንም ፈጽመው እስከሚያጠፏቸው ድረስ ሐውልቶቹን ሰባበሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጡ፥ በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኮረብታው መስገጃዎችና መሠዊያዎች አፈረሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ። 2 ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው አቆመ፤ በጌታ ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ እንዲያገለግሉ፥ እንዲያመሰግኑም ክብርም እንዲሰጡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን አቆመ። 3 በጌታም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፈለውን ወሰነ። 4 የጌታንም ሕግ በጽኑ እንዲያገለግሉ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የሚገባቸውን ድርሻ እንዲሰጡአቸው በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ። 5 ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን ጠጅ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ ሁሉ በብዛት ሰጡ፤ የሁሉንም አሥራት በብዛት አቀረቡ። 6 በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳም ልጆች የበሬውንና የበጉን አሥራት፥ ለአምላካቸውም ለጌታ የተቀደሰውን አሥራት አመጡ፥ ከምረውም አስቀመጡት። 7 በሦስተኛው ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ። 8 ሕዝቅያስና ሹማምንቱም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ ጌታንና ሕዝቡን እስራኤልን ባረኩ። 9 ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ። 10 ከሳዶቅም ወገን የሆነ ታላቁ ካህን ዓዛርያስ፦ “ሕዝቡ ቁርባኑን ወደ ጌታ ቤት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፥ ጠግበናልም፥ ጌታ ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ የተረፈውም ይህ ክምር ትልቅ ነው” ብሎ ተናገረ። ካህናቱና ሌዋውያኑ ዳግመኛ መዋቀራቸው 11 ሕዝቅያስም በጌታ ቤት ውስጥ ግምጃ ቤት እንዲያዘጋጁ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ። 12 ቁርባኑና አሥራቱን የተቀደሱትንም ነገሮች በታማኝነት ወደዚያ አስገቡ። ሌዋዊውም ኮናንያ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕረግ ሁለተኛ ነበረ፤ 13 በንጉሡም በሕዝቅያስና በጌታ ቤት አለቃ በዓዛርያስ ትእዛዝ ይሒዒል፥ ዓዛዝያ፥ ናሖት፥ አሣሄል፥ ይሬሞት፥ ዮዛባት፥ ኤሊኤል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስ፥ ከኮናንያና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ። 14 የሌዋዊውም የይምና ልጅ የምሥራቁ ደጅ ጠባቂ ቆሬ የጌታን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያከፋፍል ሕዝቡ ለጌታ በፈቃድ ባቀረቡት መባ ላይ ተሾመ። 15 በካህናቱም ከተሞች ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ድርሻቸውን በታማኝነት እንዲሰጡ ዔድን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማያ፥ አማርያ፥ ሴኬንያ የቆሬ ረዳቶች ነበሩ። 16 በትውልዳቸው ከተቈጠሩት በቀር ዕድሜያቸው ሦስት ዓመት የሆናቸውና ከዚያ በላይ የሆኑ በየሰሞናቸውም ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ ጌታ ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፤ 17 በየአባቶቻቸውም ቤት ካህናቱ ተቈጠሩ፤ በየሥርዓታቸውና በየሰሞናቸው ዕድሜያቸው ሀያ ዓመት የሆናቸውና ከዚያ በላይ የሆኑ ሌዋውያኑ ተቈጠሩ። 18 በታማኝነትም ቅድስናቸውን ጠብቀዋልና ካህነናቱ በየትውልዳቸው ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከወንዶችና ከሴቶች ልጆቻቸው እንዲሁም ከማኅበሩ ሁሉ ጋር ተቈጠሩ። 19 በየከተማይቱም ሁሉ በከተማቸው መሰማሪያዎች ውስጥ ላሉ ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ ከካህናቱም ወገን ላሉ ወንዶች ሁሉ፥ በትውልዳቸውም ለተቈጠሩ ሌዋውያን ሁሉ ድርሻቸውን እንዲሰጡአቸው በስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ። 20 ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በጌታ ፊት መልካምንና ቅንን ነገር እውነትንም አደረገ። 21 ስለ ጌታም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም፥ አምላኩን ለመፈለግ በፍጹም ልቡ አደረገው፥ ተከናወነለትም። |