Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ስለ ደማስቆ የተነገረ ትንቢት። እነሆ፥ ደማስቆ ከተማነቷ ይቀራል፤ የፍርስራሽም ክምር ትሆናለች።

2 ከተሞችዋ ለዘለዓለም ባድማ ይሆናሉ፤ ለመንጋ ማሰማርያ ይሆናሉ፤ መንጎች በዚያ ያርፋሉ የሚያስፈራቸውም የለም።

3 ምሽግም ከኤፍሬም፥ መንግሥትም ከደማስቆ ይወገዳል፤ የሶርያም ትሩፍ እንደ እስራኤል ልጆች ክብር ይሆናል፤ ይላል የሠራዊት ጌታ።

4 በዚያን ቀን የያዕቆብ ክብር ይደበዝዛል፥ የሰውነቱም ውፍረት ይመነምናል።

5 አጫጅ የቆመውን እህል በእጁ ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ፥ በራፋይም ሸለቆ እንደሚለቀም ቃርሚያ ይሆናል።

6 የወይራ ዛፍ ሲያራግፉት በቅርንጫፉ ራስ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት ፍሬ ችፍግ ባለው ቅርንጫፍ ላይ እንደሚገኝ፥ እንዲሁ ጥቂት ቃርሚያ ይቀራል፥ ይላል ጌታ የእስራኤል አምላክ።

7 በዚያ ቀን ሰዎች ወደ ፈጣሪያቸው ይመለከታሉ፤ ዐይኖቻቸውም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ።

8 በእጃቸውም ወደ ሠሯቸው መሠዊያዎች አይመለከቱም፤ በጣቶቻቸው ወዳበጇቸው የዕጣን መሠዊያዎች ወይም ወደ ማምለኪያ ዐምዶች አይመለከቱም።

9 በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ምክንያት የአሞራውያንና የኤዊያውያን ከተሞች ምድረ በዳ እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ጠንካራ ከተሞችህ ባድማም ይሆናሉ።

10 አዳኝ አምላክህን ረስተሃል፤ መሸሸጊያ ዐለትህንም አላሰብክም፤ ስለዚህ ያማረውን ተክል ብትተክልም እንግዳንም ዘር ብትዘራ፥

11 በተከልክበት ቀን እንዲበቅል፥ በዘራህበት ማግስት እንዲያብብ ብታደርግ እንኳን፥ ነገር ግን በኀዘንና በብርቱ ደዌ ቀን መከሩ እንዳልነበር ይሆናል።

12 እንደ ባሕር ሞገድ ለሚተም የብዙ ሕዝቦች ጩኸት፥ እንደ ኃያል የውኃ ሞገድ የሚያስገመግም ድምጽ ለሚያሰሙ ሕዝቦች ወዮላቸው!

13 ሕዝቦች እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ይጮኻሉ፤ እርሱ ግን ይገሥጻቸዋል፤ እነርሱም እየሸሹ ይርቃሉ፤ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ በነፋስ ፊት፥ ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረውም ትቢያ ይበተናሉ።

14 በመሸ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሽብር አለ! ከመንጋቱም በፊት አንዳቸውም አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፥ የበዘበዙንም ዕጣ ይህ ነው።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos