ዕብራውያን 1:2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ግን፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን፥፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አሁን ግን በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ሁሉን ነገር ወራሽ ባደረገው በልጁ አማካይነት ለእኛ ተናገረን፤ ዓለምንም ሁሉ የፈጠረው በእርሱ ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፥ ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ |
በዘመኑም ፍጻሜ፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጎርፋሉ።
ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ ጌታ እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?
ሰማያትን የፈጠረ ጌታ፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፦ እኔ ጌታ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።
ምድርን እንደሚሸፍን ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፥ በአንተ በኩል ቅድስናዬን በፊታቸው በምገልጥበት ጊዜ፥ አሕዛብ እንዲያውቁኝ፥ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።
ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን ጌታንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን ፈርተው ወደ ጌታና ወደ መልካምነቱ ይመጣሉ።
እንዲህም ይሆናል፥ በመጨረሻው ዘመን የጌታ ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶች በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
እርሱም ገና እየተናገረ ሳለ እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ እነሆ ከደመናው ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የተወደደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ።
ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።
“እግዚአብሔር ይላል ‘በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤
ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ከእርሱ ጋር የክብሩ ተካፋዮች እንድንሆን ከእርሱ ጋር መከራ ብንቀበል የእግዚአብሔር ወራሾችና ከክርስቶስም ጋር አብረን ወራሾች ነን።
ነገር ግን፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር ተሰውሮም የነበረውን እንናገራለን።
ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ እግዚአብሔር አብ አለን፤ እንዲሁም ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።
እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንደምትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ ዐውቃለሁና። በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ስለምትፈጽሙ፥ እጆቻችሁ በሠሯቸውም ነገሮች እርሱን ስለምታስቆጡት በሚመጡት ዘመናት ጥፋት ይደርስባችኋል።”
እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ ይህንኑ አረጋግጠውልናል።
አባትና እናት የትውልድም ሐረግም የሉትም፤ ለዘመኑም መጀመሪያ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።
እንዲህ ቢሆን ኖሮ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።