ዘፍጥረት 49 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ያዕቆብ ምስክርነት 1 ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፦ “በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብስቡ። 2 እናንት የያዕቆብ ልጆች ተሰብሰቡ፥ ስሙም፥ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ። 3 ሮቤል፥ አንተ በኩር ልጄና ኃይሌ፥ የጉብዝናዬም መጀመሪያ፥ የክብር አለቃና የኃይል አለቃ። 4 እንደ ውኃ የምትዋልል፥ አለቅነት ለአንተ አይሁን፥ ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና፥ አረከስኽውም፥ ወደ አልጋዬም ወጣ። 5 ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፥ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። 6 በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፥ ከጉባኤአቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፥ በቁጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና። 7 ቁጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፥ ኩርፍታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፥ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ። 8 ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፥ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፥ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ። 9 ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፥ ልጄ ሆይ፥ ከአደንህ ወጣህ፥ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፥ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል? 10 በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፥ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል። 11 ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፥ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፥ ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም። 12 ዓይኑም ከወይን ይቀላል፥ ጥርሱም ከወተት ይነጻል። 13 ዛብሎን በባሕር ዳር ይቀመጣል፥ እርሱም ለመርከቦች ወደብ ይሆናል፥ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ድረስ ነው። 14 ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፥ በበጎች ጉረኖም መካከል ያርፋል። 15 ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ፥ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን፥ ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ አደረገ፥ በከባድ ጉልበት ሥራ አገልጋይ ሆነ። 16 ዳን በወገኑ ይፈርዳል፥ ከእስራኤል ነገድ እንደ አንዱ። 17 ዳን በጐዳና ላይ እንደ እባብ ይሆናል፥ በመንገድም እንደ ቀንዳም እባብ፥ ፈረሱን ከሰኮናው ይነክሳል፥ ፈረሰኛም ወደ ኋላው ይወድቃል። 18 ጌታ ሆይ፥ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ። 19 ጋድን ዘማቾች ይዘምቱበታል፥ እርሱ ግን ተከታትሎ ይዘምትባቸዋል። 20 የአሴር እንጀራው ወፍራም ነው፥ ለነገሥታቱም ደስ የሚያሰኝ መብልን ይሰጣል። 21 ንፍታሌም የተፈታ ሚዳቋ ነው፥ መልካም ቃልን ይሰጣል። 22 ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፥ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ። 23 ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፥ 24 ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፥ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥ 25 በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት። 26 የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፥ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረብቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፥ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ። 27 ብንያም ነጣቂ ተኩላ ነው፥ የበዘበዘውን በጥዋት ይበላል፥ የማረከውንም በማታ ይካፈላል።” 28 እነዚህም ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፥ አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው፥ ባረካቸውም፥ እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው። የያዕቆብ የመጨረሻ ሰዓት እና ሞት 29 እንዲህ ብሎም አዘዛቸው፦ “እኔ ወደ ወገኖቼ እሰበሰባለሁ፥ በኬጢያዊ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፥ 30 እርሷም በከነዓን ምድር ከመምሬ በስተ ምሥራቅ በኩል በማክፌላ የሚገኘው ነው፤ አብርሃም ይህ ዋሻ የሚገኝበትን እርሻ ለመቃብር ቦታ የገዛው ከሒታዊው ከዔፍሮን ነው።” 31 አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ፥ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ከዚያ ተቀበሩ፥ ከዚያም እኔ ልያን ቀበርኋት፥ 32 እርሻውና በእርሷ ላይ ያለችው ዋሻ ከኬጢ ልጆች የተገዙ ናቸው። 33 ያዕቆብም ትእዛዙን ለልጆቹ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ እግሮቹን በአልጋ ላይ ሰብስቦ ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። |