ሮሜ 8:29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ልጁ በብዙዎች ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቶአቸዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፥ ይህም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህም የሆነበት ምክንያት አስቀድሞ ያወቃቸው ልጁን እንዲመስሉና ልጁም ከብዙ ወንድሞች መካከል በኵር እንዲሆን እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ወሰነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ |
ሙሴም እግዚአብሔርን፥ “እነሆ፥ አንተ፦ ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም ከሁሉ ይልቅ ዐወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ።
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ይህን ያልኸኝን ነገር አደርግልሃለሁ፤ በፊቴ ሞገስን አግኝተሀልና ከሁሉ ይልቅ ዐውቄሃለሁና”አለው።
እኔን የወደድህበት ፍቅር በእነርሱ ይኖር ዘንድ፥ እኔም በእነርሱ እኖር ዘንድ ስምህን ነገርኋቸው፤ ደግሞም እነግራቸዋለሁ፤”
ጌታችን ኢየሱስም፥ “አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞች ሂጂና፦ ወደ አባቴ፥ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ፥ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው” አላት።
እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝቡን አልጣላቸውም፤ ኤልያስ እስራኤልን ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በከሰሳቸው ጊዜ መጽሐፍ ያለውን አታውቁምን?
ዳግመናም የክብሩን ባለጠግነት ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ ለወደዳቸውና ለጠራቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የምሕረት መላእክትን ያመጣል።
ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔር ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።
እኛስ ሁላችን ፊታችንን ገልጠን በመስተዋት እንደሚያይ የእግዚአብሔርን ክብር እናያለን፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ተሰጠን መጠን የእርሱን አርአያ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንገባለን።
እርሱም እንደ ከሃሊነቱ ረዳትነት መጠን የተዋረደውን ሥጋችንን የሚያድሰው፥ ክቡር ሥጋዉንም እንዲመስል የሚያደርገው፥ የሚያስመስለውም፥ ሁሉም የሚገዛለት ነው።
ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፤ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ፥ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፤
ሆኖም “ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፤” ደግሞም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዐመፅ ይራቅ፤” የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል።
ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፤ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።
ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።