አሞጽ 9:5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ ይዳስሳል፤ ያነዋውጣታልም፤ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ግድያ እንደ ወንዝ ይፈስሳል፤ ደግሞም እንደ ግብፅ ወንዝ ይወርዳል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ጌታ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ፣ ምድርን ይዳስሳል፤ እርሷም ትቀልጣለች፤ በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የምድር ሁለመና እንደ አባይ ወንዝ ይነሣል፤ እንደ ግብጽ ወንዝም ይወርዳል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ የሠራዊት አምላክ ምድርን ይዳስሳል እርሷም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ሞላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ዳግመኛም እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም መላዋ ምድር እንደ ግብጹ የዐባይ ወንዝ ከፍና ዝቅ በማለት ትናወጣለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሲነካ ትቀልጣለች፤ በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ይዳስሳል እርስዋም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፥ ሙላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ደግሞም እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች። |
በሚኖሩባት ሰዎች ክፋት ምድሪቱ የምታለቅሰውና የዱሩ ሣርስ ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቼ ነው? እግዚአብሔር ፍጻሜያችንን አያይም ብለዋልና እንስሶችና ወፎችም ጠፍተዋል።
ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ በእርስዋም ከሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፤ ከምድርም ተንቀሳቃሾች ጋር ትጠፋለች፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ።
በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርስዋም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ጦርነት እንደ ወንዝ ይፈስሳል፤ እንደ ግብፅም ወንዝ ይሞላል፤ ደግሞም ይወርዳል።