ራእይ 6:8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነሆ ግራጫ ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ይባል ነበር፤ ሲኦልም ይከተለው ነበር፤ ሞትና ሲኦልም የምድርን አንድ አራተኛ እጅ በጦርነት፥ በራብ፥ በቸነፈርና በምድር አራዊት እንዲገድሉ ሥልጣን ተሰጣቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ግራጫ ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረውም ስሙ ሞት ነበር፤ ሲኦልም ከኋላ ይከተለው ነበር። እነርሱም በሰይፍ፣ በራብ፣ በመቅሠፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አየሁም፤ እነሆም የገረጣ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አየሁም፤ እነሆም ሐመር ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። |
ልዑል እግዚአብሔር የሞትን ኀይል ለዘለዓለም ያጠፋል! ከሰዎችም ሁሉ ዐይን እንባን ያብሳል፤ ወገኖቹ በዓለም ሁሉ ላይ የተቀበሉትን ኀፍረት ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ራሱ ይህን ተናግሮአል።
እየጾሙ ቢጸልዩ እንኳ አላዳምጣቸውም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ሆነ የእህል ቊርባን ቢያቀርቡልኝ እንኳ በእነርሱ ደስ አልሰኝም፤ ይልቁንም በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ እንዲያልቁ አደርጋለሁ።”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህን ሕዝብ እንደ ዓሣ የሚያጠምዱና እንደ አውሬ የሚያድኑ ብዙ ሰዎችን እልካለሁ፤ በየተራራውና በየኰረብታው በቋጥኞች ውስጥ ባሉ ዋሻዎችም እያደኑ ይይዙአቸዋል።
ሁሉም በአሠቃቂ በሽታ ያልቃሉ፤ የሚያለቅስላቸውም ሆነ የሚቀብራቸው እንኳ አያገኙም፤ ሬሳቸው እንደ ጒድፍ በሜዳ ላይ ይከመራል፤ በጦርነትና በራብ ያልቃሉ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ ይሆናል።
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ በእነርሱ ላይ ጦርነትን፥ ራብንና ቸነፈርን ላመጣባቸው ነው፤ ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበሉት እንደማይቻል የበለስ ዛፍ ፍሬ አደርጋቸዋለሁ፤
ናቡከደነፆር መጥቶ ግብጽን ድል ይነሣል፤ በበሽታ እንዲሞቱ የተወሰነባቸው በበሽታ ይሞታሉ፤ ተማርከው እንዲወሰዱ የተወሰኑ ይማረካሉ፤ በጦርነት እንዲሞቱ የተወሰኑ በጦርነት ይገደላሉ።
አንተንና የወንዞችህን ዓሣዎች ሁሉ ወደ በረሓ እወረውራችኋለሁ፤ ሬሳህም ተነሥቶ ሳይቀበር በመሬት ላይ ወድቆ ይቀራል፤ ለወፎችና ለአራዊትም ምግብ እንዲሆን አደርገዋለሁ።
ከሕዝባችሁ አንድ ሦስተኛው እጅ በራብና በበሽታ ያልቃል፤ አንድ ሦስተኛው ከከተማው ውጪ በሰይፍ ይገደላል፤ ሌላው ሦስተኛ እጅ በአራቱ ማእዘን በነፋስ እንዲበተን አድርጌ በኋላ በሰይፍ አሳድደዋለሁ።
ከሲኦል ኀይል እታደጋቸዋለሁን? ከሞትስ አድናቸዋለሁን? ሞት ሆይ! መቅሠፍቶችህ የት አሉ? ሲኦል ሆይ! አጥፊነትህ የት አለ? እኔኮ አልራራላቸውም፤
በእርግጥ ሀብት ሰውን ያታልላል፤ ትምክሕተኛ ሰው ዕረፍት የለውም፤ እንደ መቃብር ስስታም እንደ ሞትም በቃኝ የማይል ስለ ሆነ መንግሥታትን ሁሉ ለራሱ ይወራል፤ ሕዝቦችንም ይማርካል።
አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ያልሽው ቅፍርናሆም! ወደ ሲኦል ትወርጂአለሽ! በአንቺ የተደረጉት ተአምራት፥ በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ ያቺ ከተማ ሳትጠፋ፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበር!
በጅራቱ የኮከቦችን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ ሴቲቱ በምትወልድበት ጊዜ ልጅዋን ለመዋጥ አስቦ ዘንዶው ልትወልድ ወደተቃረበችው ሴት ከፊት ለፊትዋ ቆመ፤