ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ክፉ አሳብ 1 የቀና ነገርን ሳያስቡ ራሳቸው እንዲህ አሉ፥ ሕይወታችን ጥቂት ነው፥ የሚያሳዝንም ነው-። ለሰውም ሞት መድኀኒት የለውም፥ ከመቃብርም የተመለሰ የታወቀ የለምና። 2 እኛ በከንቱ ተፈጥረናልና ከዚህም በኋላ እንዳልተፈጠርን እንሆናለን፤ በአፍንጫችን ያለ ትንፋሻችን እንደ ጢስ ነውና። በልቡናችንም እንቅስቃሴ የብልጭልጭታ ቃል አለና። 3 ከሞተ በኋላ ሥጋችን ትቢያ ይሆናል፤ መንፈሳችንም እንደ ጉም ተን ይበተናልና። 4 ስማችንም በጊዜ ይዘነጋል፤ ሥራችንንም የሚያስበው ማንም የለም፤ ሕይወታችንም እንደ ደመና ፍለጋ ያልፋል፤ እንደ ጉምም ይበተናል፤ በፀሐይ ጨረር እንደ ተበተነ፥ በሙቀቱም እንደ ቀለጠ ውርጭ ይሆናል። 5 ሕይወታችንም እንደ ጥላ ያልፋልና፥ ይህ የተወሰነ ነገር ስለሆነ ለሞታችን መከልከል የለውም፤ ማንም አይመልሰውምና። 6 ኑ ባለው መልካም ነገር ደስታን እናድርግ፤ በጐልማሳነታችንም ወራት ሳለን በመትጋት በሰውነታችን ደስ የሚያሰኘውን እናድርግ። 7 ዋጋው ብዙ የሆነ ወይን እንጠጣ፤ የሚሸት ሽቱንም እንቀባ፤ የመፀው አበባም አይለፈን። 8 ቡቃያችን ሳይጠወልግ ጽጌረዳን እንቀዳጅ፤ ከትዕቢታችን አበባ የማይሳተፍ ማንም አይኑር። 9 ከእኛ መካከል ደስታችን የማይገባው ሰው አይኑር፤ እርሱ ዕድላችን፥ ርስታችንም ነውና በየቦታው ለደስታችን ምልክት እንተው። 10 ጻድቁን ድሃ እንቀማ፤ ለባልቴቲቱም አንራራ፤ ዕድሜው ብዙ ከሆነ ከሽማግሌም ሽበት የተነሣ አንፈር። 11 ኀይላችን የጽድቅ ሕግ ይሁነን፤ ደካማ ሕሊና የተናቀ ይባላልና። 12 ኑ፤ ጻድቁን እንግደለው፤ በእኛ ጭንቅና ጽኑዕ ሆኖብናልና፥ ሥራችንንም ይቃወማልና፤ ሕግ በማጣታችንም ያሽሟጥጠናልና፥ የትምህርታችንንም በደል ይሰብካልና። 13 “እግዚአብሔርንም ማወቅ በእኔ አለ” ይላል፤ ራሱንም የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጋል። 14 ሕሊናችንንም የሚዘልፍ ሆኖብናል። 15 በመልኩም በእኛ ጭንቅ ሆኖብናል፤ አኗኗሩም ከሌላ ጋር አይመሳሰልም፤ መንገዱም ልዩ ነው። 16 በእርሱ ዘንድም የተናቅን ሆነናል፤ ከርኵሰትም እንደሚርቅ ከመንገዳችን ይርቃል። የጻድቃንን መጨረሻ ያመሰግናል፤ እግዚአብሔርም አባቱ እንደ ሆነ ይመካል። 17 ነገሩም ቀዋሚ እንደ ሆነ እንይ፥ ከመልኩም የተነሣ የሚሆነውን እንመርምር። 18 የእግዚአብሔርስ እውነተኛ ልጅ ከሆነ ያድነው፤ ከሚቃወሙትም እጅ ይታደገው። 19 ቅንነቱንም እናውቅ ዘንድ በስድብና በመከራ እንመርምረው። ትዕግሥቱንም በክፉ እንፈትነው። 20 እንደ ቃሉ ረዳት ይሆነው እንደ ሆነ የከፋና የተዋረደ ሞትን እንፍረድበት። ክፋት ልብን እንደሚያሳውር 21 ይህን ነገር አሰቡ፤ በዚህም ሳቱ፤ ክፋታቸው የልብ ዕውሮች አድርጋቸዋለችና። 22 የእግዚአብሔርን ምሥጢር አላወቁም፤ የጻድቁንም ዋጋ ተስፋ አላደረጉም፤ ነውር የሌለባቸውን የንጹሐት ነፍሳትንም ብዙ ክብር አላወቁም። 23 እግዚአብሔር ሰውን ያለ ሞት ፈጥሮታልና፥ በራሱም አምሳል ፈጥሮታልና። 24 ነገር ግን በዲያብሎስ ቅንዐት ሞት መጣ፥ ወደዚህ ዓለምም ገባ። 25 ከእርሱም ድርሻ የሆኑት ሞትን ሞከሩት። |