Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሉቃስ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)


ስለ ንስሓ

1 በዚያ ወራ​ትም ሰዎች ወደ እርሱ መጥ​ተው ጲላ​ጦስ ደማ​ቸ​ውን ከመ​ሥ​ዋ​ዕ​ታ​ቸው ጋር ስለ ቀላ​ቀ​ለው ስለ ገሊላ ሰዎች ነገ​ሩት።

2 ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ይህች መከራ ስለ አገ​ኘ​ቻ​ቸው እነ​ዚህ ገሊ​ላ​ው​ያን ከገ​ሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ተለ​ይ​ተው ኀጢ​ኣ​ተ​ኞች የሆኑ ይመ​ስ​ሉ​አ​ች​ኋ​ልን?

3 አይ​ደ​ለም፤ እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ እና​ን​ተም ንስሓ ካል​ገ​ባ​ችሁ ሁላ​ችሁ እንደ እነ​ርሱ ትጠ​ፋ​ላ​ችሁ።

4 ወይስ እነ​ዚያ በሰ​ሊ​ሆም ግንብ ተጭኖ የገ​ደ​ላ​ቸው ዐሥራ ስም​ንቱ ሰዎች ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ሰዎች ይልቅ ተለ​ይ​ተው ኀጢ​እ​ታ​ኞች ይመ​ስ​ሉ​አ​ች​ኋ​ልን?

5 አይ​ደ​ለም፤ እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ እና​ን​ተም ንስሓ ካል​ገ​ባ​ችሁ ሁላ​ችሁ እንደ እነ​ርሱ ትጠ​ፋ​ላ​ችሁ።”


ፍሬ ስለ​ሌ​ላት በለስ

6 እን​ዲ​ህም ብሎ መሰ​ለ​ላ​ቸው፥ “አንድ ሰው በታ​ወ​ቀች በወ​ይኑ ቦታ ውስጥ በለስ ነበ​ረ​ችው፤ ፍሬ​ዋን ሊወ​ስድ ወደ እር​ስዋ ሄዶ አላ​ገ​ኘም።

7 የወ​ይ​ኑን ጠባ​ቂም፦ “የዚ​ችን በለስ ፍሬ ልወ​ስድ ስመ​ላ​ለስ እነሆ፥ ሦስት ዓመት ነው፤ አላ​ገ​ኘ​ሁም፤ እን​ግ​ዲ​ህስ ምድ​ራ​ች​ንን እን​ዳ​ታ​ቦ​ዝን ቍረ​ጣት” አለው።

8 እር​ሱም መልሶ እን​ዲህ አለው፥ “አቤቱ አፈር ቈፍሬ በሥሯ እስከ አስ​ታ​ቅ​ፋት፥ ፍግም እስከ አፈ​ስ​ባት ድረስ የዘ​ን​ድ​ሮን እንኳ ተዋት።

9 ምና​ል​ባት ለከ​ርሞ ታፈራ እንደ ሆነ፥ ያለ​ዚያ ግን እን​ቈ​ር​ጣ​ታ​ለን።”


በሰ​ን​በት ቀን ስለ ዳነ​ችው ሴት

10 በሰ​ን​በ​ትም በአ​ንድ ምኵ​ራብ ውስጥ አስ​ተ​ማ​ራ​ቸው።

11 ዐሥራ ስም​ንት ዓመት ሙሉ ጋኔን ያጐ​በ​ጣት አን​ዲት ሴት ነበ​ረች፤ ጐባ​ጣም ነበ​ረች፤ ከቶ ቀጥ ብላ መቆም አት​ች​ልም ነበር።

12 ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም አይቶ ራራ​ላት፥ ጠር​ቶም፥ “ሴትዮ፥ ከደ​ዌሽ ተፈ​ት​ተ​ሻል” አላት።

13 እጁ​ንም በላ​ይዋ ጫነ፤ ያን​ጊ​ዜም ፈጥና ቀጥ አለች፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም አመ​ሰ​ገ​ነ​ችው።

14 የም​ኵ​ራቡ ሹምም ጌታ ኢየ​ሱስ በሰ​ን​በት ፈው​ሶ​አ​ልና፤ እየ​ተ​ቈጣ መልሶ ሕዝ​ቡን እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ሥራ​ች​ሁን የም​ት​ሠ​ሩ​ባ​ቸው ስድ​ስት ቀኖች ያሉ አይ​ደ​ለ​ምን? ያን​ጊዜ ኑና ተፈ​ወሱ፤ በሰ​ን​በት ቀን ግን አይ​ሆ​ንም።”

15 ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ አላ​ቸው፥ “እና​ንት ግብ​ዞች፥ እና​ን​ተሳ አህ​ያ​ች​ሁን ወይም በሬ​አ​ች​ሁን በሰ​ን​በት ቀን ገለባ ከሚ​በ​ላ​በት አት​ፈ​ቱ​ት​ምን? ውኃ ልታ​ጠ​ጡ​ትስ አት​ወ​ስ​ዱ​ት​ምን?

16 ይህቺ የአ​ብ​ር​ሃም ልጅ እነሆ፥ ሰይ​ጣን ከአ​ሰ​ራት ዐሥራ ስም​ንት ዓመት ነው፤ እር​ስ​ዋስ በሰ​ን​በት ቀን ከእ​ስ​ራቷ ልት​ፈታ አይ​ገ​ባ​ምን?”

17 ይህ​ንም ባለ ጊዜ በእ​ርሱ ላይ በጠ​ላ​ት​ነት የተ​ነ​ሡ​በት ሁሉ አፈሩ፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ከእ​ርሱ ስለ​ሚ​ደ​ረ​ገው ድንቅ ነገር ሁሉ ደስ አላ​ቸው።


ስለ ሰና​ፍጭ ቅን​ጣት ምሳሌ

18 በዚያ ቀንም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “መን​ግ​ሥተ ሰማ​ያት ምን ትመ​ስ​ላ​ለች? በም​ንስ እመ​ስ​ላ​ታ​ለሁ?

19 ሰው ወስዶ በእ​ርሻ ውስጥ የዘ​ራት የሰ​ና​ፍጭ ቅን​ጣ​ትን ትመ​ስ​ላ​ለች፤ አደ​ገች፤ ታላቅ ዛፍም ሆነች፤ የሰ​ማይ ወፎ​ችም በቅ​ር​ን​ጫ​ፎ​ችዋ ውስጥ ተጠ​ለሉ።”


ስለ እርሾ

20 ዳግ​መ​ኛም እን​ዲህ አለ፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ግ​ሥት በምን እመ​ስ​ላ​ታ​ለሁ?

21 ሴት ወስዳ ሦስት መስ​ፈ​ሪያ ዱቄት የለ​ወ​ሰ​ች​በ​ትን፥ ሁሉ​ንም እን​ዲ​ቦካ ያደ​ረ​ገ​ውን እርሾ ትመ​ስ​ላ​ለች”።


ስለ​ሚ​ድ​ኑት

22 በየ​ከ​ተ​ማ​ውና በየ​መ​ን​ደሩ እየ​ሄደ፥ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም እየ​ተ​መ​ላ​ለሰ ያስ​ተ​ምር ነበር።

23 አንድ ሰውም፥ “አቤቱ የሚ​ድኑ ጥቂ​ቶች ናቸ​ውን?” አለው። እርሱ ግን እን​ዲህ አላ​ቸው፦

24 “ወደ ጠባቡ በር ትገቡ ዘንድ በርቱ፤ እላ​ች​ኋ​ለሁ፥ ሊገቡ የሚሹ ብዙ​ዎች ናቸው፤ ግን አይ​ች​ሉም።

25 ባለ​ቤቱ ተነ​ሥቶ ደጁን ይዘ​ጋ​ልና፤ ያን​ጊዜ ከደጅ ቆመው፦ ‘አቤቱ፥ አቤቱ፥ ክፈ​ት​ልን’ እያሉ በር ሊመቱ ይጀ​ም​ራሉ፤ መል​ሶም፦ ከወ​ዴት እንደ ሆና​ችሁ አላ​ው​ቃ​ች​ሁም ይላ​ቸ​ዋል።

26 ከዚ​ህም በኋላ፦ በፊ​ትህ በላን፥ ጠጣን፥ በአ​ደ​ባ​ባ​ያ​ች​ንም አስ​ተ​ማ​ርህ ልትሉ ትጀ​ም​ራ​ላ​ችሁ።

27 እር​ሱም እን​ዲህ ይላ​ቸ​ዋል፦ እና​ንተ ከወ​ዴት እንደ ሆና​ችሁ አላ​ው​ቃ​ች​ሁም፤ ዐመ​ፅን የም​ታ​ደ​ርጉ ሁላ​ችሁ፥ ከእኔ ራቁ፤

28 አብ​ር​ሃ​ምን፥ ይስ​ሐ​ቅ​ንና ያዕ​ቆ​ብን፥ ነቢ​ያ​ት​ንም ሁሉ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት በአ​ያ​ች​ኋ​ቸው ጊዜ እና​ን​ተን ወደ ውጭ ያወ​ጡ​አ​ች​ኋል፤ በዚ​ያም ልቅ​ሶና ጥርስ ማፋ​ጨት ይሆ​ናል።

29 ከም​ሥ​ራ​ቅና ከም​ዕ​ራብ፥ ከሰ​ሜ​ንና ከደ​ቡብ ይመ​ጣሉ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መን​ግ​ሥት በማ​ዕድ ይቀ​መ​ጣሉ፤

30 ኋለ​ኞች ፊተ​ኞች ይሆ​ናሉ፤ ፊተ​ኞ​ችም ኋለ​ኞች ይሆ​ናሉ።”


ስለ ሄሮ​ድስ

31 በዚ​ያ​ችም ቀን ከፈ​ሪ​ሳ​ው​ያን ወገን ሰዎች መጥ​ተው፥ “ከዚህ ውጣና ሂድ፤ ሄሮ​ድስ ሊገ​ድ​ልህ ይሻ​ልና” አሉት።

32 እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ሂዱና ያችን ቀበሮ እን​ዲህ በሉ​አት፤ እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋ​ን​ን​ትን አወ​ጣ​ለሁ፤ ሕይ​ወ​ት​ንም አድ​ላ​ለሁ፤ በሦ​ስ​ተ​ኛ​ውም ቀን እፈ​ጽ​ማ​ለሁ።

33 ዛሬና ነገስ አለሁ፤ በሦ​ስ​ተ​ኛው ቀን ግን እሄ​ዳ​ለሁ፤ ነቢይ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም እንጂ በውጭ ሊሞት አይ​ገ​ባ​ው​ምና።


ስለ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም መፈ​ታት

34 “ነቢ​ያ​ትን የም​ት​ገ​ድ​ሊ​ያ​ቸው፥ ወደ አንቺ የተ​ላ​ኩ​ትን ሐዋ​ር​ያ​ት​ንም የም​ት​ደ​በ​ድ​ቢ​ያ​ቸው ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም፥ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም፥ ዶሮ ጫጩ​ቶ​ች​ዋን ከክ​ን​ፍዋ በታች እን​ደ​ም​ት​ሰ​በ​ስብ ልጆ​ች​ሽን ልሰ​በ​ስ​ባ​ቸው ምን ያህል ወደ​ድሁ? ነገር ግን እንቢ አላ​ችሁ።

35 እነሆ፥ ቤታ​ችሁ ምድረ በዳ ሆኖ ይቀ​ር​ላ​ች​ኋል፤ ከዛሬ ወዲያ ‘በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስም የሚ​መጣ ቡሩክ ነው’ እስ​ክ​ትሉ ድረስ እን​ደ​ማ​ታ​ዩኝ እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች