Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለእስራኤል ብርሃን እንደ ወጣላቸው 1 በጻድቃንህ ዘንድ ግን ታላቅ ብርሃን ነበር፥ እነዚያ ቃላቸውን ይሰሙ ነበርና፥ መልካቸውን ግን አያዩም ነበርና። 2 እነዚያ የሚወዷቸውን ይደበድቧቸው ነበርና፤ የተበደሉትንም መከራ ስለ አጸኑባቸው እርስ በርሳቸው ይመሰጋገኑ ነበር። 3 እነዚህ ግን በተላከላቸው የማዳን ስጦታ ደስ አላቸው፥ የማይታወቅ ጎዳናንም ይመራቸው ዘንድ የእሳት ዐምድን ሰጣቸው፥ በሚወደደውም መንገድ የማያቃጥል ፀሐይን ሰጣቸው። 4 ብርሃንን ያጡ ዘንድ፥ በጨለማም ይታሰሩ ዘንድ ለእነዚያ ይገባቸዋል፤ ለዓለም ይሰጥ ዘንድ ያለው፥ የማያልፍ የሕግህ ብርሃን ያላቸው ልጆችህን አስረው አግዘዋቸዋልና። የግብፃውያን የበኵር ልጆች ሞት 5 የጻድቃን ልጆችን ይገድሉ ዘንድ ባሰቡና በመከሩ ጊዜ፥ ለዘለፋ ሊሆንባቸው አንዱ ሕፃን ተጥሎ ዳነ። በእርሱም ብዙዎች ልጆቻቸውንና ማኅበራቸውን ሁሉ ያለ ርኅራኄ በብዙ ውኃ አጠፋህ። 6 የተማማሉባትን መሐላ ባወቁ ጊዜ፥ በፍቅር ያስቧት ዘንድ አባቶቻችን ያቺን ሌሊት ዐወቋት። 7 ለጻድቃን ሕዝብህ ደኅንነትን፥ ለተቃዋሚዎች ጠላቶችም ጥፋትን ሰጠህ። 8 የሚቃረኑትን እንዳጠፋሃቸው፥ እንዲሁ የጠራኸንን እኛን አክብረኸናልና። 9 አገልጋዮችህ ጻድቃን ያማረ መሥዋዕትን ይሠዉ ነበረና፥ በመስማማትም የጌትነትህን ሕግ በልቡናቸው አሳድረዋልና በዚህ አምሳል ቅዱሳን መልካሙን ነገር ተቀበሉ፥ መከራውም ለሚገባቸው ነው። አባቶቻችን ግን የምስጋናውን መዝሙር በደስታ ይዘምሩ ነበር። 10 ነገራቸው ሳይተባበር ከጠላቶች ልቅሶ ጩኸት ጋር ቃላቸው ይገናኝ ነበር። እናቶችም ስለ ልጆቻቸው የልቅሶውን ድምፅ ያደምጡ ነበር። 11 የባሪያውም ቅጣት ከጌታው ጋር በመቅሠፍት ተካከለ። ጭፍራውንና ንጉሡንም ይህች መከራ እኩል አገኘቻቸው። 12 ሁሉም በአንድነት በአንድ አምሳል ሞቱ፤ ቍጥር የሌላቸው የሞቱ ሰዎች በድኖችም ነበሩ። በአንዲት ሰዓት የከበረች ፍጥረታቸው ፈጽማ ስለ ጠፋች ሕያዋን የሞቱትን ሰዎች ይቀብሯቸው ዘንድ አልቻሉምና። 13 ስለ ሟርታቸውም የመጣባቸውን መቅሠፍት ሁሉ አላወቁምና በበኸር ልጃቸው መጥፋት ሕዝቡ የእግዚአብሔር ልጆች እንደ ሆኑ ዐወቁ። 14 ፍጹም ጸጥታ ፍጥረትን ሁሉ በሸፈነ ጊዜ፥ ሌሊቷም በፍጥነቷ መካከል ሳለች፥ 15 ሁሉን የሚችል ቃልህ እንደ ድል አድራጊና ጦረኛ ሆኖ፥ ከሰማያት ከዙፋንህ ውስጥ ወደ ጥፋት ምድር መካከል ወረደ። 16 አድልዎ የሌለባት ትእዛዝህንም እንደ ተሳለ ሰይፍ ታጥቆ፥ በመካከላቸውም ቆሞ አውራጃዎቻቸውን ሁሉ በሞት ሞላ፥ ሰማይንም ነካ፤ በምድርም ቁሞ ነበር። 17 ያንጊዜም በአስፈሪዎች ሕልሞች ምትሀት አወካቸው፥ ያላሳቧት ድንጋጤም በላያቸው ሠለጠነችባቸው። 18 ከእነርሱም እኩሌታው የሞተ ሆኖ በሌላ ቦታ የሚወድቅ ነበረ፥ የሚሞቱባትንም ምክንያት ገለጠላቸው። 19 ክፉ ነገር ስለምን እንደሚያገኛቸውና እንደሚያጠፋቸውም ባለማወቅ እንዳይሆኑ ያወኳቸው ሕልሞች አስቀድመው ይህን ነግረዋቸዋልና። በእስራኤል ላይ ስለ ታዘዘው መቅሠፍት አሮን እንደ ጸለየ 20 ከጻድቃንም አስቀድሞ ለሞት የሚያበቃ መከራ ያገኛቸው አሉ። በምድረ በዳም መቅሠፍት ሆነ፥ ከእነርሱም ብዙዎችን አጠፋ። ነገር ግን መቅሠፍቱ ብዙ ዘመን አልዘገየም። 21 ነውር የሌለበት ሰው ጸሎት የሚጸልይበትን፥ ዕጣንም የሚያጥንበትን የአገልግሎት መሣሪያ፥ ልብሰ መትከፉን ይዞ ፈጥኖ ተዋግቶአልና ኀጢአታቸውን ለማቃለል ባለሟልነትን አገኘ፤ መዓቱን ተቃወመ፥ መቅሠፍቱንም ጸጥ አደረገ። በዚህም ያንተ መልእክተኛ እንደ ሆነ ራሱን አስታወቀ። 22 አጥፊዎችንም አሸነፈ፤ በሥጋዊ ኀይል ወይም በጦር መሣሪያ አይደለም፤ ነገር ግን የአባቶችን መሐላና ቃል ኪዳናቸውን በማሰብ ቀሣፊውን በቃልህ አስወገደ። 23 ብዛታቸው የማይቈጠር የሞቱ ሰዎች እርስ በርሳቸው በወደቁ ጊዜ በበሽተኞቹና በሕያዋኖቹ መካከል ቁሞ መቅሠፍቱን ጸጥ አደረገ። ለሕያዋንም መንገድን ለየ። 24 የዓለሙ ክህነት ሁሉ በልብሱ ጫፍ ላይ ነበርና፥ ባሕርይ በሚባሉ ዕንቍዎች አራት ዙሪያዎች የተቀረጸው የአበውም ክብር በጫንቃው ላይ ነበርና፥ የአንተም ልዕልና በራሱ አክሊል ላይ ነበርና። 25 በዚህም የሚያጠፉ ቸነፈሮች ራቁ፥ እነዚህ ሥራዎችም አስፈሯቸው፥ ነገር ግን መቅሠፍቱ ብቻ በበቃ ነበር። |