ዘሌዋውያን 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ሰባተኛ ዓመት ዕረፍት ( ዘዳ. 15፥1-11 ) 1 እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ እኔ የምሰጣችሁ ምድር ታርፋለች፤ ለእግዚአብሔርም ሰንበት ታደርጋለች። 3 ስድስት ዓመት እርሻህን ትዘራለህ፤ ስድስት ዓመትም ወይንህን ትቈርጣለህ፤ ፍሬዋንም ትሰበስባለህ። 4 በሰባተኛው ዓመት ግን ሰንበት ነው፤ የምድር ዕረፍት ነው፤ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው፤ እርሻህን አትዝራ፤ ወይንህንም አትቍረጥ። 5 የምድራችሁን ገቦ አትጨደው፤ የተቀደሰውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ዓመት ይሆናል። 6 የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን። 7 ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ ምግብ ይሁን። ዐመተ ኢዮቤልዩ 8 “የዓመታትን ሰባት ሰንበቶች ሰባት ጊዜ ሰባት ለራስህ ትቈጥራለህ፤ እነዚህም ሰባት የዓመታት ሱባዔያት አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ። 9 ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር ከወሩ በዐሥረኛው ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ። 10 አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፤ በምድሪቱም ለሚኖሩት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ። 11 ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፤ የገቦውንም አትጨዱ፤ የተቀደሰውንም በእርሱ አትልቀሙ። 12 ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ። 13 “በዚች ኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል። 14 ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያስጨንቀው። 15 ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይከፍልሃል። 16 እንደ ዓመታቱ ብዛት ዋጋውን ያበዛል፤ እንደ ዓመታቱም ማነስ ዋጋውን ያሳንሳል፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል። 17 እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያስጨንቅ፤ ነገር ግን አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ። 18 “ሥርዐቴንም አድርጉ፤ ፍርዴንም ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። 19 ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። 20 እናንተም፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥ 21 እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። 22 በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፤ ከከረመውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከከረመው እህል ትበላላችሁ። የዕዳ ምሕረት ዐመት 23 “ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም በእኔ ፊት እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘለዓለም አትሽጡ። 24 በርስታችሁም ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ አድርጉ። 25 ወንድምህም ቢደኸይ፥ ከርስቱም ቢሸጥ፥ ለእርሱ የቀረበ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል። 26 የሚቤዠውም ሰው ቢያጣ፥ እርሱም እጁ ቢረጥብ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥ 27 የሽያጩን ዘመን ቈጥሮ የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ። 28 ለራሱም ዕዳውን መክፈል ባይችል፥ ሽያጩ በገዛው ሰው እጅ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቀመጥ፤ በኢዮቤልዩም ዓመት ይውጣ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ። 29 “ሰውም ቅጥር ባለበት ከተማ መኖርያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት መቤዠት ይችላል። 30 አንድ ዓመት እስኪጨረስ ባይቤዠው ቤቱ ለገዡ ይሆናል፤ ቅጥር ባለበት ከተማ ያለውን ያን ቤት ይመረምሩለታል፤ ለገዛው ሰው ለልጅ ልጁ ለዘለዓለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩ ዓመትም አይወስዱበትም። 31 ቅጥር በሌለበት መንደር ያሉ ቤቶች ግን እንደ እርሻ ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፤ በኢዮቤልዩ ዓመትም ይመለሳሉ። 32 የሌዋውያንን ከተሞች፥ በከተሞቻቸውም ያሉ ቤቶቻቸውን ሌዋውያን ለዘለዓለም መቤዠት ይችላሉ። 33 ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የሌዋውያን ከተሞች ቤቶች ርስቶቻቸው ናቸውና በርስቱ ከተማ ያለ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ዓመት ይመለሳል። 34 በከተማዎቻቸው ዙሪያ ያሉ እርሻዎቻቸውም የዘለዓለም ርስቶቻቸው ናቸውና አይሸጡም። ለድኃ በወለድ አለማበደር 35 “ከአንተ ጋር ያለው ወንድምህ ቢደኸይ፥ እጁም በአንተ ዘንድ ቢደክም እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛ ትረዳዋለህ፤ ከአንተም ጋር ይኑር። 36 ወንድምህ ከአንተ ጋር ይኖር ዘንድ ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 37 ብርህን በወለድ አታበድረው፤ እህልህንም በትርፍ አትስጠው። 38 የከነዓንን ምድር እሰጥህ ዘንድ፥ አምላክም እሆንህ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና። ስለ ባሪያ ነጻነት 39 “ወንድምህ ቢቸገር፥ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባሪያ አድርገህ አትግዛው። 40 እንደ ምንደኛና እንደ ስደተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ያገልግልህ። 41 በኢዮቤልዩ ዓመትም እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ይወጣል፤ ወደ ወገኖቹም፥ ወደ አባቱም ርስት ይመለሳል። 42 ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎች ናቸውና ባሪያ እንደሚሸጥ አይሸጡ። 43 በሥራ አታስጨንቀው፤ ነገር ግን አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ። 44 ምን ያህል ወንድ ባሪያና ሴት ባሪያ እንዲኖሩህ ብትፈልግ ግን በዙሪያችሁ ካሉት ከእነርሱ ከአሕዛብ ወንድና ሴት ባያሪያዎችን ግዙ። 45 በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት ስደተኞች ልጆች ለራሳችሁ ትገዛላችሁ፤ ከዘመዶቻቸውም በምድራችሁ የሚኖሩት ሁሉ ለርስታችሁ ይሁኑአችሁ። 46 ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ ታወርሱአቸዋላችሁ፤ እነርሱም ለእናንተ ለዘለዓለም ውርስ ይሆናሉ፤ ነገር ግን ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤል ልጆች ማናቸውም ሰው ወንድሙን በሥራ አያስጨንቀው። 47 “በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው፥ ወይም ለእንግዳው ወይም ለወገኖቹ ዘር ቢሸጥ፥ 48 ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤ 49 ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ ለእርሱ የቀረበ ዘመድ ይቤዠው፤ ወይም እርሱ እጁ ቢረጥብ ራሱን ይቤዠው። 50 ከገዛውም ሰው ጋር ከገዛበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቍጠር፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሁን፤ እንደ ምንደኛውም ዘመን ከእርሱ ጋር ይሁን። 51 ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 52 እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂት ዓመታት ቢቀሩ እንደ ዓመቱ ይቍጠሩለት፤ እንደ ኣመታቱም መጠን የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 53 በየዓመቱ እንደ ምንደኛ ከእርሱ ጋር ይኑር፤ በፊትህ እንደ ቀደመው አያስጨንቀው። 54 በዚህ ዘመን ሁሉ ግን ባይቤዥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ይውጣ። 55 የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባሪያዎች ናቸውና፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎች ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። |