ዘሌዋውያን 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ካህናት ቅድስና 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፥ “ከወገናቸው በሞተ ሰው ራሳቸውን እንዳያረክሱ ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ንገራቸው። 2 ከቅርብ ዘመዶቻቸው፥ ከአባቶቻቸው፥ ወይም ከእናቶቻቸው፥ ወይም ከወንዶች ልጆቻቸው፥ ወይም ከሴቶች ልጆቻቸው፥ ወይም ከወንድሞቻቸው፥ 3 ወይም ከቀረበች ያላገባች ድንግል እኅት በቀር ራሳቸውን አያርክሱ። 4 ራሱን ያጐሰቍል ዘንድ ከሕዝቡ በማንም አይርከስ። 5 ስለ ሞተው ሰው ራሳቸውን አይላጩ፤ ጢማቸውንም አይላጩ፤ ሥጋቸውንም አይንጩ። 6 ለአምላካቸው ቅዱሳን ይሁኑ፤ የአምላካቸውንም ስም አያርክሱ፤ የእግዚአብሔርን መሥዋዕትና የአምላካቸውን መባ ያቀርባሉና ቅዱሳን ይሁኑ። 7 ለአምላኩ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም ከባልዋ የተፋታችውን አያግባ። 8 የአምላክህን መባ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሁንልህ። 9 የካህንም ሰው ልጅ በግልሙትና ራስዋን ብታረክስ በግልሙትና አባቷን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል። 10 “በራሱም ላይ የቅባት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ፥ ከወንድሞቹ የተለየው ካህን ራሱን አይላጭ፤ ልብሱንም አይቅደድ። 11 ወደ ሞተ ሰው ሁሉ አይግባ፤ በአባቱም ወይም በእናቱ አይርከስ። 12 የአምላኩም ቅባት ዘይት ቅዱስነት በላዩ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፤ የአምላኩንም ቅዱስ ስም አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13 እርሱም ከወገኑ ድንግል ሴትን ያግባ። 14 ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፋታችውን፥ የተጠላችውን ወይም ጋለሞታዪቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከወገኑ ድንግሊቱን ያግባ፤ 15 እኔም የምቀድሰው እግዚአብሔር ነኝና በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያጐስቍል።” 16 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 17 “ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ከወገንህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን መባ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። 18 ንጹሕ ያልሆነ ሰው ሁሉ አይቅረብ፤ ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም ጆሮ ቈራጣ፥ 19 ወይም እጀ ሰባራ፥ ወይም እግረ ሰባራ፥ 20 ወይም ጎባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዐይነ መጭማጫ፥ ወይም ቅንድበ መላጣ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም የአባለዘሩ ፍሬ አንድ የሆነ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። 21 ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን መባ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። 22 የቅዱሱንና የቅዱሰ ቅዱሳኑን የአምላኩን መባ ይብላ፤ 23 ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶችን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፤ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝና።” 24 ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ነገራቸው። |