ዘፀአት 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)5፥ የእንስሳት ዕልቂት 1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደ ፈርዖን ገብተህ እንዲህ በለው፦ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2 ሕዝቤን ልትለቃቸው እንቢ ብትል፥ ብትይዛቸውም፥ 3 እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ በአሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም፥ በአህዮችም፥ በግመሎችም፥ በበሬዎችም፥ በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ይኸውም እጅግ ጽኑዕ ሞት ነው፤ 4 በዚያ ጊዜም በግብፃውያን ከብቶችና በእስራኤል ልጆች ከብቶች መካከል ልዩነት አደርጋለሁ። ከእስራኤልም ልጆች ከብቶች አንዳች አይሞትም።” 5 እግዚአብሔርም፥ “ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል ብሎ ጊዜን ወሰነ።” እግዚአብሔርም ያን ነገር በነጋው አደረገ፤ 6 የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም። 7 ፈርዖንም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ እንዳልሞተ በአየ ጊዜ ልቡ ደነደነ፤ ሕዝቡንም አልለቀቀም። 6፥ ሻህኝ 8 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን፥ “እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፤ ሙሴም በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። 9 እርሱም በግብፅ ሀገር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፤ በግብፅም ሀገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻህኝ የሚያመጣ ቍስል ይሆናል” አላቸው። 10 ሙሴም አመዱን በፈርዖን ፊት ወስዶ ወደ ሰማይ በተነው፤ በሰውና በእንስሳም ላይ ሻህኝ የሚያወጣ ቍስል ሆነ። 11 ጠንቋዮችም ቍስል ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ ቍስል ጠንቋዮችንና ግብፃውያንን ሁሉ ይዞአቸው ነበርና። 12 እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እግዚአብሔርም ለሙሴና ለአሮን እንደ ተናገረው አልሰማቸውም። 7፥ በረዶ 13 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ማልደህ ተነሣ፤ በፈርዖንም ፊት ቆመህ እንዲህ በለው፦ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንዲያመልኩኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 14 በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ፥ በአገልጋዮችህም፥ በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ በዚህ ጊዜ እልካለሁ። 15 አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን እመታሃለሁ፤ ሕዝብህንም እገድላቸዋለሁ፤ ምድራችሁም ትመታለች። 16 ነገር ግን ኀይሌን እገልጥብህ ዘንድ፥ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ ጠበቅሁህ። 17 አንተ ግን እንዳትለቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህ፤ 18 እነሆ፥ ከተመሠረተች ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ በግብፅ ሆኖ የማያውቅ እጅግ ታላቅ በረዶ ነገ በዚህ ጊዜ አዘንባለሁ። 19 አሁን እንግዲህ ፥ ከብቶችህንም በሜዳም ያለህን ሁሉ ፈጥነህ ሰብስብ። በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንስሳ ሁሉ በረዶ ወርዶበት ይሞታልና።” 20 ከፈርዖን ሹሞች የእግዚአብሔርን ቃል የፈራ ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ ሰበሰበ። 21 የእግዚአብሔርን ቃል በልቡ ያላሰበ ግን ከብቶቹን በሜዳ ተወ። 22 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ በግብፅም ሀገር ሁሉ በሰውና በእንስሳም በምድርም ቡቃያ ሁሉ ላይ በረዶ ይሆናል።” 23 ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጐድጓድና በረዶ ላከ፤ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ ሀገር ሁሉ ላይ በረዶ አዘነበ። 24 በረዶም ነበረ፤ በበረዶውም መካከል እሳት ይቃጠል ነበር፤ በረዶውም በግብፅ ሀገር ሁሉ ሕዝብ ከኖረበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚች ቀን እንደ እርሱ ያልሆነ እጅግ ብዙና ጠንካራ ነበረ። 25 በረዶውም በግብፅ ሀገር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ሰውንና እንስሳን መታ፤ በረዶውም የእርሻን ቡቃያ ሁሉ መታ። የጫካውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። 26 የእስራኤል ልጆች ተቀምጠው በነበሩባት በጌሤም ሀገር ብቻ በረዶ አልወረደም። 27 ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን ጠራ፤ “አሁንም በደልሁ፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን ኀጢአተኞች ነን። 28 እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ የአምላክ ነጐድጓድ፥ በረዶውም፥ እሳቱም ጸጥ ይላል፤ እኔም እለቅቃችኋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ከዚህ አትቀመጡም” አላቸው። 29 ሙሴም፥ “ለፈርዖን ከከተማ በወጣሁ ጊዜ እጄን ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱም ለእግዚአብሔር እንደ ሆነች ታውቅ ዘንድ ነጐድጓዱ ጸጥ ይላል፤ በረዶውም፥ ዝናቡም ደግሞ አይወርድም። 30 ነገር ግን አንተና ሹሞችህ እግዚአብሔር አምላክን ምንጊዜም እንደማትፈሩ አውቃለሁ” አለው። 31 ተልባውና ገብሱ ተመታ፤ ገብሱ አሽቶ፥ ተልባውም አፍርቶ ነበርና። 32 ስንዴውና አጃው ግን አልተመቱም፤ ገና ቡቃያ ነበሩና። 33 ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፤ እጁንም ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጐድጓዱም፥ በረዶውም ጸጥ አለ፤ ዝናቡም በምድር ላይ አላካፋም። 34 ፈርዖንም ዝናቡ፥ በረዶውም፥ ነጐድጓዱም ጸጥ እንደ አለ በአየ ጊዜ በደልን ጨመረ፤ እርሱና ሹሞቹም ልባቸውን አደነደኑ። 35 የፈርዖንም ልብ ጸና፤ እግዚአብሔርም በሙሴ አፍ እንደ ተናገረ የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም። |