ሐዋርያት ሥራ 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጳውሎስ ጕዞ ወደ ኢየሩሳሌም 1 ከእነርሱም ከተለየን በኋላ እኛ በመርከብ ተሳፍረን፥ መንገዳችንንም አቅንተን ወደ ቆስ መጣን፤ በበነጋውም ወደ ሮዶስ፥ ከዚያም ወደ ጳጥራ ገባን። 2 ወደ ፊንቄም የሚያልፍ መርከብ አግኝተን በዚያ ላይ ተሳፍረን ሄድን። 3 ቆጵሮስንም አየናት፤ በስተ ግራችንም ትተናት ወደ ሶርያ ሄድን፤ ወደ ጢሮስም ወረድን፤ በመርከብ ያለውን ጭነት ሁሉ በዚያ ያራግፉ ነበርና። 4 በዚያም ደቀ መዛሙርትን አገኘንና በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ነገሩት። 5 ከዚህም በኋላ ለመሄድ ወጣን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን። 6 እርስ በርሳችንም ተሳስመን ተሰነባበትን፤ ከዚህም በኋላ ወደ መርከብ ወጣን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። 7 እኛም ከጢሮስ ወጥተን አካ ወደምትባል ሀገር መጣን፤ ወንድሞቻችንንም አግኝተን ሰላም አልናቸው፤ በእነርሱም ዘንድ አንድ ቀን አደርን። 8 በማግሥቱም ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ ወደ ወንጌላዊው ወደ ፊልጶስ ቤትም ገባን፤ እርሱም ከሰባቱ ወንድሞች ዲያቆናት አንዱ ነው። 9 ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። 10 በእርሱም ዘንድ ብዙ ቀን ኖርን፤ ከይሁዳም አጋቦስ የሚባል አንድ ነቢይ ወረደ። 11 ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ እጁንና እግሩን በገዛ እጁ አስሮ እንዲህ አለ፥ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ የዚህን መታጠቂያ ጌታ አይሁድ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።” 12 ይህንም ሰምተን የሀገሪቱን ሰዎች ይዘን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ጳውሎስን ማለድነው። 13 ጳውሎስ ግን መልሶ፥ “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? እያለቀሳችሁ ልቤን ትሰብሩታላችሁ፤ እኔ እኮ ተስፋ የማደርገው መከራንና እግር ብረትን ብቻ አይደለም፤ እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞትም ቢሆን የቈረጥሁ ነኝ” አለ። 14 እንቢ ባለ ጊዜም ዝም አልን፤ እኛም እግዚአብሔር የፈቀደው ይሁን ብለን ተውነው። 15 ከእነዚያም ቀኖች በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። 16 ከደቀ መዛሙርትም ከቂሳርያ አብረውን የመጡ ነበሩ፤ ሄደንም ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ወገን ከሆነው በቆጵሮስ በሚኖረው በምናሶን ቤት አደርን። 17 ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜም ወንድሞቻችን በደስታ ተቀበሉን። 18 በማግሥቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ገባ፤ ቀሳውስትም ሁሉ በዚያ ነበሩ። 19 ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ሐዋርያነት እግዚአብሔር በአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ ነገራቸው። 20 እነርሱም ሰምተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉ፥ “ወንድማችን ሆይ፥ ከአይሁድ መካከል ያመኑት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህን? ሁሉም ለኦሪት የሚቀኑ ናቸው። 21 ነገር ግን የማይሆነውን እንደምታስተምር፥ የሙሴንም ሕግ እንደምታስተዋቸው፥ በአሕዛብ መካከል ያሉ ያመኑ አይሁድንም ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፥ የኦሪትንም ሕግ እንዳይፈጽሙ እንደምትከለክላቸው ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። 22 አሁንሳ ምን ይሁን? ሕዝቡ ወደዚህ እንደ መጣህ ይሰሙና ይሰበሰቡ ይሆናል። 23 ስለዚህም ይህን የምልህን አድርግ፦ ብፅዐት ያላቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። 24 ይዘሃቸው ሂድ፤ ከእነርሱም ጋር ራስህን አንጻ፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ ስለ እነርሱ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ የሚያሙህም በሐሰት እንደ ሆነ፥ አንተም የኦሪትን ሕግ እንደምትጠብቅ ሁሉም ያውቃሉ። 25 ስለሚአምኑት አሕዛብ ግን እርም ከሆነውና ለጣዖታት ከሚሠዉት፥ ከዝሙት፥ ሞቶ የተገኘውንና ደምን ከመብላት እንዲከለከሉ እኛ አዝዘናል።” 26 ያንጊዜም ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር ነጻ። የመንጻታቸውንም ወራት መድረሱን ከነገራቸው በኋላ ሁሉም እየአንዳንዳቸው መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞአቸው ገባ። ጳውሎስ ስለ መከሰሱ 27 በሰባተኛውም ቀን ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በመቅደስ አዩት፤ ሕዝቡንም ሁሉ በእርሱ ላይ አነሳሥተው ያዙት። 28 እየጮሁም እንዲህ አሉ፥ “እናንተ የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ ርዱን፤ በየስፍራው ሕዝባችንን፥ ኦሪትንም፥ ይህንም ስፍራ የሚቃወም ትምህርት ለሰው ሁሉ የሚያስተምር እነሆ፥ ይህ ሰው ነው፤ አሁንም አረማውያንን ወደ መቅደስ አስገባ፤ ቤተ መቅደስንም አረከሰ። 29 የኤፌሶን ሀገር ሰው የሆነ ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና፤ ጳውሎስም ወደ ቤተ መቅደስ ያስገባው መስሎአቸው ነበርና። 30 ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ሄደው ጳውሎስን ጐትተው ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ በሩንም ሁሉ ዘጉ። 31 ሊገድሉትም ፈልገው ብዙ ደበደቡት፤ ወዲያውም ኢየሩሳሌም በመላዋ እንደ ታወከች የሚገልጥ መልእክት ወደ ሻለቃው ደረሰለት። 32 በዚያ ጊዜም ጭፍሮቹን ከአለቆቻቸው ጋር ይዞ ወደ እነርሱ ሄደ፤ እነርሱም የሻለቃውን ጭፍሮች ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታታቸውን ተዉ። 33 የሻለቃውም ቀረብ ብሎ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር አዘዘ፤ “ምንድነው? ምንስ አደረገ?” ብሎም ጠየቀ። 34 ሕዝቡም እኩሌቶቹ እንዲህ ነው፤ እኩሌቶቹም እንዲህ አይደለም እያሉ ይጮሁ ነበር፤ ሻለቃውም ሕዝቡ የሚታወክበትን ርግጡን ማወቅ ተሣነው፤ ወደ ወታደሮቹም ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። 35 ደረጃውንም በሚወጣበት ጊዜ ወታደሮች ተሸክመው አወጡት፤ ሰው ይጋፋ ነበርና። 36 ብዙዎችም ይከተሉት ነበር፤ ሕዝቡም፥ “አስወግዱት” እያሉ ይጮሁ ነበር። ጳውሎስ ስለ ራሱ እንደ ተከላከለ 37 ወደ ሰፈርም በደረሰ ጊዜ ጳውሎስ ሻለቃውን፥ “ላነጋግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው፤ ሻለቃውም፥ “የጽርዕ ቋንቋ ታውቃለህን?” አለው። 38 “ምናልባት ከዚህ በፊት ወንጀል የሠራህና ከነፍሰ ገዳዮች አራት ሺህ ሰዎችን ይዘህ ወደ ምድረ በዳ የወጣህ ያ ግብፃዊ አንተ አይደለህምን?” አለው። 39 ጳውሎስም፥ “እኔስ አይሁዳዊ ሰው ነኝ፤ የተወለድሁባትም ሀገር ጠርሴስ የታወቀች የቂልቅያ ከተማ ናት፤ ለሕዝቡም እንድነግራቸው ትፈቅድልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። 40 በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ እጁን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ፤ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ ጳውሎስ በዕብራይስጥ ቋንቋ ተናገረ፤ እንዲህም አለ። |