1 ነገሥት 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ንጉሥ ዳዊት እንደ ሸመገለ 1 ንጉሡ ዳዊትም አረጀ፤ ዘመኑም አለፈ፤ ልብስም ይደርቡለት ነበር፤ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር። 2 የዳዊት አሽከሮችም፥ “ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ልጅ ትፈለግለት፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፥ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ትቀፈው፤ ታሙቀውም” አሉ። 3 በእስራኤልም ሀገር ሁሉ የተዋበች ቆንጆ ፈለጉ፤ ሱነማዪቱን አቢሳንም አገኙ፤ ወደ ንጉሡም ወሰዱአት። 4 ቆንጆዪቱም እጅግ ውብ ነበረች፤ ንጉሡንም ታቅፈውና ታገለግለው ነበር፤ ንጉሡ ግን አያውቃትም ነበር። አዶንያስ ለመንገሥ እንደ ሞከረ 5 የአጊትም ልጅ አዶንያስ፥ “ንጉሥ እሆናለሁ” ብሎ ተነሣ፤ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎችን አዘጋጀ። 6 አባቱም፥ “ከቶ ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?” ብሎ አልከለከለውም ነበር፤ እርሱም ደግሞ መልኩ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ፤ እርሱንም ከአቤሴሎም በኋላ ወልዶት ነበር። 7 ሴራውም ከሶርህያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ነበረ፤ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር። 8 ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነቢዩም ናታን፥ ሳሚም፥ ሬሲም፥ የዳዊትም ኀያላን አዶንያስን አልተከተሉም ነበር። 9 አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን፥ ጠቦቶችንም በሮጌል ምንጭ አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ፤ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም አገልጋዮች፥ የይሁዳንም ኀያላን ሁሉ ጠራ። 10 ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኀያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም። ሰሎሞን እንደ ነገሠ 11 ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት፥ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን? 12 አሁንም ነዪ፤ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኚ እመክርሻለሁ። 13 ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለአገልጋይህ፦ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ አልማልህልኝምን? ስለምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው። 14 እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፤ ቃልሽንም አጸናለሁ።” 15 ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ ወደ እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፤ ሱነማዪቱም አቢሳ ንጉሡን ታገለግለው ነበር። 16 ቤርሳቤህም አጎንብሳ ለንጉሡ ሰገደች፤ ንጉሡም፥ “ምን ሆንሽ?” አላት። 17 እርስዋም አለችው፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ ለአገልጋይህ፦ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ በአምላክህ ምለህልኝ አልነበረምን? 18 አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፤ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፤ 19 እርሱም ብዙ በሬዎችንና ጠቦቶችን፥ በጎችንም ሠውቶአል፤ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ ባሪያህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም። 20 አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዐይን ይመለከትሃል። 21 ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ንጉሥ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኀጢአተኞች እንቈጠራለን።” 22 እነሆም፥ እርስዋ ከንጉሡ ጋር ስትነጋገር ነቢዩ ናታን መጣ፤ 23 ለንጉሡም፥ “እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቶአል” ብለው ነገሩት፤ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግንባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ። 24 ነቢዩ ናታንም አለ፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፦ አንተ ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔ ላይም ይቀመጣል ብለሃልን? 25 እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ጠቦቶችን፥ በጎችንም ሠውቶአል፤ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊቱን አለቃ ኢዮአብን፥ ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፤ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ፦ አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ ይላሉ። 26 ነገር ግን እኔን አገልጋይህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ አገልጋይህንም ሰሎሞንን አልጠራም። 27 በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነገር ነውን? ለአገልጋይህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ለምን አልነገርኸውም?” 28 ንጉሡም ዳዊት፥ “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፤ በንጉሡም ፊት ቆመች። 29 ንጉሡም እንዲህ ብሎ ማለ፥ “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን! 30 በእውነት፦ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፤ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ።” 31 ቤርሳቤህም በግንባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ ሰገደችና፥ “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘለዓለም በሕይወት ይኑር” አለች። 32 ንጉሡም ዳዊት፥ “ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩ ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። 33 ወደ ንጉሡም ገቡ። ንጉሡም አላቸው፥ “የጌታችሁን አገልጋዮች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፤ 34 በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ቀብተው ያንግሡት፤ መለከትም ነፍታችሁ፦ ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ በሉ። 35 በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፤ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፤ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፤ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ ይነግሥ ዘንድ አዝዣለሁ።” 36 የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፥ “እንዲሁ ይሁን፤ የጌታዬም የንጉሥ አምላክ እግዚአብሔር ይህን ያጽና። 37 እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሥ ጋር እንደ ነበረ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፤ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሡ ከዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርግ።” 38 ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፤ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን ወሰዱት። 39 ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የዘይቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፤ መለከትም ነፋ፤ ሕዝቡም ሁሉ፥ “ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ” አሉ። 40 ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፤ ከበሮንና መሰንቆንም መቱ፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች። 41 አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፤ ኢዮአብም የመለከት ድምፅ በሰማ ጊዜ፥ “ይህ በከተማ የምሰማው ድምፅ ምንድን ነው?” አለ። 42 እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፤ አዶንያስም፥ “አንተ ኀያል ሰው ነህና፥ መልካምም ታወራልናለህና ግባ” አለው። 43 ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ፥ “በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው። 44 ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ላከ፤ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት። 45 ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን ቀብተው በግዮን አነገሡት፤ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፤ ከተማዪቱም አስተጋባች፤ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው። 46 ሰሎሞንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል። 47 የንጉሡም አገልጋዮች ገብተው፦ ‘እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ይልቅ መልካም ያድርግ፤ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ’ ብለው ጌታቸውን ንጉሡ ዳዊትን መረቁ፤” ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ። 48 ንጉሡም፥ “ዐይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን ዘር የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን” አለ። 49 አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፤ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ። 50 አዶንያስም ከሰሎሞን ፊት የተነሣ ፈራ፤ ተነሥቶም ሄደ፤ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ። 51 ለሰሎሞንም፥ “እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ፦ ንጉሡ ሰሎሞን አገልጋዩን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል” አሉት። 52 ሰሎሞንም፥ “እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደ ሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጕር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፤ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደ ሆነ ይሞታል” አለ። 53 ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፤ ከመሠዊያውም አወረዱት፤ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን ሰገደ፤ ሰሎሞንም፥ “ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። |