Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አንደኛ ራእይ 1 ከተማችን ኢየሩሳሌም በጠፋች በሠላሳ ዓመት ዕዝራ የተባልሁ እኔ ሱቱኤል በባቢሎን ነበርሁ፤ በመኝታዬም ደንግጬ ነበርሁ፤ ፊቴም ተገልጦ ነበር። በልቡናዬም ዐሳቤ ይወጣና ይወርድ ነበር። 2 የጽዮንን ጥፋትዋን፥ በባቢሎንም የሚኖሩ ሰዎችን ደስታ አይቻለሁና። 3 ሰውነቴም ፈጽማ ታወከች፤ የሚያስፈራ ነገርንም ከልዑል ጋር እናገር ጀመርሁ። 4 ስናገርም እንዲህ አልሁ፥ “አቤቱ፥ ጌታ ሆይ፥ አስቀድሞ ምድርን በፈጠርሃት ጊዜ አንተ ብቻህን ይህን ያልህ አይደለምን? አዳምን በመዋቲ ሥጋ ታስገኘው ዘንድ መሬትን ያዘዝሃት አይደለምን? 5 እርሱም የእጆችህ ፍጥረት ነው፥ በእርሱም ላይ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አልህበት፤ በፊትህም ሕያው ሆነ። 6 ምድርም ሳትጸና ቀኝህ ወደ ተከለቻት ወደ ገነት አገባኸው። 7 እርሱንም የጽድቅ ትእዛዝን አዘዝኸው፤ ትእዛዝህንም አፈረሰ፤ ከዚህም በኋላ በእርሱና በልጆቹ ላይ ሞትን አመጣህ፤ አሕዛብና ሕዝብ፥ ነገድና ቍጥር የሌላቸው መንደረተኞችም ከእርሱ ተወለዱ። 8 አሕዛብም ሁሉ በየሥራቸው ኖሩ። በፊትህም በደሉ፤ አንተንም ካዱ፤ አንተ ግን አልከለከልሃቸውም። 9 ዳግመኛም በጊዜው ጊዜ በምድር ላይና በዚህ ዓለም በሚኖሩ ሰዎች ላይ የጥፋት ውኃን አመጣህ፤ አጠፋሃቸውም። 10 ቅጣታቸውም የተካከለ ሆነ፤ በአዳም ላይ ሞትን እንዳመጣህ እንደዚሁ በእነዚህም ላይ የጥፋት ውኃን አመጣህ። 11 ከእነርሱም ስሙ ኖኅ የሚባል አንድ ሰውን ከቤተ ሰቡ ጋር አተረፍህ፤ ከእርሱም ጻድቃንና ኃጥኣን ተወለዱ። 12 “ከዚህም በኋላ ይበዙ ዘንድ፥ በምድር የሚኖሩትም ይመሏት ዘንድ በጀመሩ ጊዜ፥ ልጆቻቸውም በበዙና ከእነርሱም ብዙ የሚሆኑ አሕዛብና ሕዝብ በተወለዱ ጊዜ፥ ከቀደመው በደል ይልቅ እንደገና እጅግ ይበድሉ ጀመሩ። 13 ከዚህም በኋላ በፊትህ በበደሉ ጊዜ ከእነርሱ አንዱን ስሙ አብርሃም የሚባለውን መረጥህ። 14 እርሱንም ወደድኸው፤ የዘመኑንም መጨረሻ ለብቻው በብቻህ በሌሊት አሳየኸው። 15 የዘለዓለም ቃል ኪዳንንም አጸናህለት፤ ልጆቹንም እስከ ዘለዓለም ፈጽመህ እንዳታጠፋቸው ተስፋ ሰጠኸው። ይስሐቅንም ሰጠኸው፤ ለይስሐቅም ያዕቆብንና ኤሳውን ሰጠኸው። ያዕቆብንም ለራስህ ለየህ፤ ኤሳውን ግን ጠላህ፤ ያዕቆብም ትልቅ ሕዝብ ሆነ፤ 16 ዘሮቹንም ከግብፅ ባወጣሃቸው ጊዜ ወደ ደብረ ሲና ወሰድሃቸው፤ 17 ሰማያትን ዝቅ አደረግህላቸው፤ ምድርንም አነዋወጥህላቸው፤ ዓለምንም አወክህላቸው፤ ጥልቁን አነዋወጥህላቸው፤ ባሕሩንም ከፈልህላቸው። 18 ለያዕቆብ ልጆች ሕግን፥ ለእስራኤልም ወገኖች ትእዛዝን ትሰጣቸው ዘንድ የእሳትና የንውጽውጽታ፥ የበረድና የነፋስ የሚሆኑ አራቱ የጌትነትህ ተአምራት ተደረጉ። 19 ነገር ግን በእነርሱ የሕግህ ፍሬ ይደረግ ዘንድ ከእነርሱ ክፉ ዐሳብን አላራቅህም። ቀዳማዊ አዳም ክፉ ልብን ገንዘብ አድርጎ ነበርና ድል ተነሣ። 20 እርሱ ብቻ አይደለም፤ ከእርሱ የተወለዱ ልጆችም ሁሉ እንጂ። 21 ከዚህም በኋላ ያች ደዌ ከሕግህ ጋር በሰዉ ሁሉ ልቡና ከክፉ ሥራ ጋር ኖረች፤ በጎነትም ጠፋች፤ ክፋት ግን ኖረች። 22 ዘመን ዐለፈ፤ ዓመትም ተፈጸመ፤ ስሙ ዳዊት የሚባል አገልጋይህንም አስነሣህ። 23 ለስምህ ከተማህን ይሠራ ዘንድ፥ መባህንም በውስጥዋ ያቀርብ ዘንድ ነገርኸው። 24 ብዙ ዓመትም ሆነ፤ ምንም የሚሠሩት በጎ ሥራ ሳይኖር በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች በደሉ። 25 አዳም እንደ አደረገ፥ ልጆቹም ሁሉ እንዳደረጉ እነርሱም ክፉ ዐሳብን ገንዘብ አድርገዋልና። 26 ከተማህንም በጠላቶችህ እጅ አሳልፈህ ሰጠህ።” ባቢሎን ከጽዮን ጋር እንደ ተገዳደረች 27 ያንጊዜ እኔ በልቡናዬ የጽዮን ከተማን እጅ ያደርጓት ዘንድ በባቢሎን የሚኖሩ ሰዎች ጽድቅን በመሥራት በውኑ ይበልጡናልን? አልሁ። 28 ከዚህም በኋላ ወደዚህ በደረስሁ ጊዜ ቍጥር የሌለው ኀጢአትን አየሁ፤ እነሆ፥ ለሠላሳ ዓመት ሰውነቴ ብዙ ከሓድያንን አየች፤ በዚህም ልቡናዬ አደነቀ። 29 ኃጥኣንን እንዴት እንደምትታገሣቸው፥ ለዝንጉዎችም እንደምትራራላቸው፥ ወገኖችህንም ጥለህ ጠላቶችህን እንዴት እንደምትጠብቅ አየሁ። 30 የማንንም አልተመለከትህም፤ የዚችስ መንገድ ፍጻሜዋ እንዴት ነው? ጽድቅን በመሥራት ባቢሎን ከጽዮን የምትበልጥበት አለን? 31 አዎ፥ ከእስራኤል ሌላ ወገን ያወቀህ አለን? ወይስ በሕግህ እንደ ያዕቆብ የታመነ ሌላ ወገን አለን? 32 ዋጋው ያልተገለጠ፥ ድካሙም ያላፈራ አለን? ወደ አሕዛብም በሄድሁ ጊዜ ሕግህንና ትእዛዝህን ሳያስቡ ደስ ብሏቸው አገኘኋቸው። 33 አሁንም በእርሱ ዘንድ የሚዛን ውልብልቢትን የምትመስል ያህል አንሶ ይገኝ እንደ ሆነ የእኛንና በባቢሎን የሚኖሩ ሰዎችን ኀጢአት በሚዛን መዝን። 34 በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች በፊትህ ያልበደሉ መቼ ነው? ወይስ ሕግህን እንደዚህ የጠበቀ ወገን ማነው? 35 ፍጹም የሆነ ሕዝብስ አይገኝም። |