ሕዝቅኤል 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሊመጣ የቀረበው ጥፋት 1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፦ ፍጻሜ! በአራቱም የምድሪቱ ማዕዘናት ላይ ፍጻሜ መጥቷል። 3 አሁን ፍጻሜ በአንቺ ላይ ነው፥ ቁጣዬን በአንቺ ላይ እሰድዳለሁ፥ እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፥ ርኩሰትሽንም ሁሉ እመልስብሻለሁ። 4 ዓይኔ አይራራልሽም እኔም አላዝንም፤ መንገድሽን በአንቺ ላይ እመልስብሻለሁ፥ ርኩሰቶችሽም በመካከልሽ ይሆናሉ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 5 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በክፋት ላይ ክፋት እነሆ፥ ይመጣል። 6 ፍጻሜ መጥቷል፥ ፍጻሜ መጥቷል፥ በአንቺ ላይ ነቅቷል፥ እነሆ፥ መጥቷል። 7 በምድር የምትኖር ሆይ፥ ፍጻሜህ ወደ አንተ መጥቷል፥ ጊዜው መጥቷል፥ ቀኑ ቀርቧል፥ የሽብር ነው እንጂ በተራራ ላይ ያለ እልልታ አይደለም። 8 አሁን በቅርብ መዓቴን በአንቺ ላይ አፈስሳለሁ፥ ቁጣዬን በአንቺ ላይ እፈጽማለሁ፥ እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፥ ርኩሰትሽንም ሁሉ እመልስብሻለሁ። 9 ዓይኔም አይራራም፥ እኔም አላዝንም፥ መንገድሽን በአንቺ ላይ እመልስብሻለሁ፥ ርኩሰቶችሽም በመካከልሽ ይሆናሉ፥ የምቀሥፍም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 10 እነሆ ቀኑ፥ እነሆ መጥቷል፥ ፍጻሜህ መጥቷል፥ ብትሩ አብቧል፥ ትዕቢትም አቆጥቁጦአል። 11 ሁከት ወደ ክፋት ብትርነት አደገ፥ ከእነርሱ፥ ከብዛታቸው፥ ከሀብታቸውም አንድም አይቀርም፥ ከመካከላቸው የሚልቅም የለም። 12 ጊዜው መጥቷል፥ ቀኑ ቀርቧል፥ የሚገዛ ደስ አይበለው የሚሸጥም አያልቅስ፥ ቁጣ ብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና። 13 በሕይወት እስካሉ ድረስ ሻጭ ወደሸጠው ነገር አይመለስ፥ ስለ ብዙዎቹ የተነገረው ራእይ አይመለስምና፥ ማንም ሰው በኃጢአቱ ሕይወቱን ማዳን አይችልም። 14 መለከቱን ነፍተዋል ሁሉንም ነገር አዘጋጅተዋል፥ ነገር ግን ወደ ጦርነት የሚሄድ የለም፥ ቁጣዬ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና። 15 ሰይፍ በውጭ፥ ቸነፈርና ራብም ከቤት አለ፥ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፥ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይበላዋል። 16 ከእነርሱም የሚሸሹ ያመልጣሉ፥ እንደ ሸለቆ እርግቦች በተራራ ላይ ይሆናሉ፥ ሁሉም በኃጢአታቸው ላይ ያቃስታሉ። 17 እጆች ሁሉ ይዝላሉ፥ ጉልበቶችም ሁሉ እንደ ውኃ ይፈስሳሉ። 18 ማቅ ይለብሳሉ፥ ድንጋጤም ይሸፍናቸዋል፥ በሁሉም ፊቶች ላይ እፍረት ይሆናል፥ ራሳቸውም ሁሉ መላጣ ይሆናል። 19 ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ፥ ወርቃቸውም እንደ ርኩስ ነገር ይቆጠራል፥ በጌታ የመዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም። አይጠግቡም፥ ሆዳቸውንም አይሞሉም፥ የኃጢአታቸው ዕንቅፋት ሆኖአልና። 20 የጌጦቻቸውን ውበት ወደ ትዕቢት ለወጡ፥ የርኩሰታቸውን ምስሎችና አስከፊ ነገሮችን ሰሩባቸው፥ ስለዚህ እኔም ይህንን ለእነርሱ ርኩስ ነገር አደርገዋለሁ። 21 በባዕድም እጅ ለዝርፊያ፥ በምድር ላሉ ክፉዎች እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እነርሱም ያረክሱአታል። 22 ፊቴን ከእነርሱ እመልሳለሁ፥ እነርሱም የተከበረ ቦታዬን ያረክሳሉ፥ ወንበዴዎችም ይገቡባታል ያረክሱአታልም። 23 ምድር በደም ፍርድ ተሞልታለች፥ ከተማም በዓመፅ ተሞልታለችና፥ ሰንሰለት ሥራ። 24 ከአገሮች ሁሉ ክፉዎችን አመጣለሁ፥ ቤቶቻቸውንም ይወርሳሉ፥ የኃያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፥ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ። 25 ጭንቀት መጥቷል፥ ሰላምም ይሻሉ፥ አይገኝምም። 26 በጥፋት ላይ ጥፋት ይመጣል፥ ወሬም ወሬን ይከተላል፥ ከነቢይ ራእይን ይፈልጋሉ፥ ከካህን ሕግ፥ ከሽማግሌዎችም ምክር ይጠፋል። 27 ንጉሡ ያለቅሳል፥ ልዑሉም ውርደትን ይለብሳል፥ የምድሪቱም ሕዝቦች እጆች ይንቀጠቀጣሉ፥ እንደ መንገዳቸው መጠን አደርግባቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። |