1 የምትሞቱበትን ቀን አስቡ፤ ነፍሳችሁ ከሥጋችሁ በምትለይበት ጊዜ፥ ገንዘባችሁንም ለሌላ በምትተዉበት ጊዜ፥ ወደማታውቁትም መንገድ በምትሄዱበት ጊዜ የምትመጣባችሁን አስቧት። 2 የሚቀበሏችሁም ክፉዎች ናቸው፤ በመልካቸውም ጥፉዎች ናቸው፤ በግርማቸውም የሚያስፈሩ ናቸው፤ ቃላችሁን አይሰሙም፤ ቃላቸውንም አትሰሙም። 3 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ስለ አላደረጋችሁ በለመናችኋቸው ጊዜ አይመልሱላችሁም፤ ስለዚህም እጅግ ያስፈሯችኋል። 4 አጋንንት ይፈሯቸዋልና የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሚፈጽሙ ሰዎች ግን ፍርሀት የለባቸውም። በኃጥኣን ነፍሳትም አጋንንት ይዘባበቱባቸዋል። 5 ይህን ዓለም ስለ ናቁት እጅግ ደስ ያሰኛቸዋልና የጻድቃን ሰዎች ነፍሳት በመላእክት ይባቤ ደስ ይላቸዋል፤ የኃጥኣን ነፍሳትን ግን ክፉዎች መላእክት ይቀበሏቸዋል። 6 የጻድቃንን ነፍሳት ያረጋጓቸው ዘንድ ከእግዚአብሔር ይላካሉና፥ የጻድቃንንና የደጋጎች ነፍሳትን የምሕረት መላእክት ይቀበሉአቸዋል። የኃጥኣንን ነፍሳት ግን ክፉዎች አጋንንት ይቀበሏቸዋል፤ በኃጥኣን ነፍሳት ይዘባበቱባቸው ዘንድ ከዲያብሎስ ይላካሉና። 7 ኃጥኣን ወዮላችሁ፤ የምትሞቱባት ቀን ሳትደርስባችሁ ለራሳችሁ አልቅሱ፤ ከሞታችሁ በኋላ ያለፈው ዘመናችሁ አይመለስም። 8 ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ፊት በደረሳችሁ ጊዜ ያለ መከራና ያለ ደዌ በደስታ ትኖሩ ዘንድ ዘመናችሁ ሳያልፍ በአላችሁበት ንስሓ ግቡ። 9 ከእግዚአብሔር ወደሚያርቅ ከንቱ ፈቃድ እንዳይስባችሁ፥ በእናንተ ጽኑ ነቀፋና መቀማጠል፥ መብልንና ደስታንም መውደድ አይገኝባችሁ፤ ያለ ልክ የጠገበች ሰውነት የእግዚአብሔርን ስም አታስብምና የዲያብሎስ መንፈስ ያድርባታል እንጂ በእርስዋ የሕይወት መንፈስ አያድርባትም። 10 ሙሴ፥ “ያዕቆብ በልቶ ጠገበ ወፈረም፥ ሰባ፥ ሰፋም፥ የፈጠረው እግዚአብሔርንም ተወው፤ 11 ሕይወቱም ከእግዚአብሔር ራቀ” ብሎ እንደ ተናገረ፥ ያለ ልክ የሆድ ጥጋብ እንዳለሌ ፈረስ መሆን ነውና፥ ያለ ልክ መብላትና መጠጣት፥ ማመንዘርም እንደ ምድረ በዳ እሪያ መሆን ነውና። 12 በልክ የሚበላ ግን በእግዚአብሔር መሠረት የጸና ይሆናል፤ እንደ አድማስም ድንጋይ፥ አጥርም እንዳለው ግንብ ይጸናል። “ኀጢአተኛ የሚያባርረው ሳይኖር ይሸሻል” ተብሎአልና። 13 ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ተዘልሎ ይኖራል። 14 እግዚአብሔርን የማይወዱ ሰዎች ግን ቃሉን አይጠብቁም፤ ልቡናቸውም የቀና አይደለም። 15 እግዚአብሔርም በምድር ሳሉ እንዳያርፉ በመንቀጥቀጥና በፍርሀት፥ ገንዘባቸውንም በመንጠቅ፥ ቍጥርም በሌለው ብዙ መከራ ተይዘው ከጌቶቻቸው እጅ እጃቸውን በሰንሰለት ታስረው፥ 16 ከመከራውም ያረፉ እንዳይሆኑ፥ አኗኗራቸውም በሰላም እንዳይሆን በተለያዩ የሚያስደነግጡ መከራዎች ሳሉ ኀዘንንና ድንጋጤን ያመጣባቸዋል። |