Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የፈጠረህን ዕወቀው፤ ያጸናህና ያዳነህ የእስራኤልን ቅዱስም አትርሳው፤ አንተ መሬት ስትሆን በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮሃልና ደስ ይልህ ዘንድ፥ ምድርንም ትቈፍራት ዘንድ በገነት አኖረህ። 2 ትእዛዙንም ባፈረስህ ጊዜ ከዚያ ከገነት አሜከላና እሾህ ወደምታበቅል፥ በአንተም ምክንያት ወደ ረገማት ወደዚች ምድር አወጣህ። 3 አንተ ምድር ነህና፥ እርስዋም ምድር ናትና፥ አንተ ትቢያ ነህና፥ እርስዋም ትቢያ ናትና፥ አንተ መሬት ነህና እርስዋም መሬት ናትና ከእርስዋም ትመገባለህ፤ ወደ እርስዋም ትመለሳለህ፤ ያስነሣህ ዘንድ እስኪወድድ ድረስ ትቢያ ትሆናለህና የሠራኸውን በደልና ኀጢአት ሁሉ ይመረምርሃልና። 4 ያንጊዜ የምትመልሰውን ዕወቅ፤ በዚህም ዓለም የሠራኸውን ክፉውንና በጎውን አስብ፤ ክፉው ይበዛ እንደ ሆነ፥ ወይም በጎው ይበዛ እንደ ሆነ መዝን፤ ምከርም። 5 በጎ ነገርንም ብታበዛ፥ ሙታን በሚነሡበት ቀን ደስ ይልህና ሐሤት ታደርግ ዘንድ ለአንተ መልካም ይሆንልሃል። 6 ክፉ ሥራን ብታበዛ ግን ወዮልህ፤ እንደ እጅህ ሥራና እንደ ልቡናህ ክፋት ፍዳህን ትቀበላለህና በባልንጀራህ ክፉ እንደ ሠራህበት፥ እግዚአብሔርንም እንዳልፈራኸው እንደ ሥራህ ፍዳህን ትቀበላለህና። 7 ባልንጀራህንም ብትከዳው፥ በእግዚአብሔርም ስም በሐሰት ብትምል፥ እንደ ሥራህ ፍዳህን ትቀበላለህና። 8 ለባልንጀራህ በማስመሰል ቃልህን በሐሰት እውነተኛ እንዲሆን ታደርጋለህና፤ አንተ ግን ሐሰት እንደ ተናገርህ ታውቀዋለህ። 9 ከአንተ ጋራ ያሉትንም እያሳመንህ ቃልህ እውነት እንደ ሆነ ታጸናለህ፤ እውነት ያልሆነ ነገርንም ታበዛለህ፤ እንደ ሥራህም ፍዳህን ትቀበላለህ፤ የማትሰጠውን ለባልንጀራህ እሰጥሃለሁ እያልህ ባልንጀራህን ትከዳዋለህ። 10 በንጹሕ ልቡናህም እሰጣለሁ ባልህ ጊዜ አጋንንት እንደ ውሾች ደጅ ይጠኑሃል፤ ሁሉንም ያስረሱሃል፤ ብትነሣም፥ ትሰጥ ዘንድ ብትወድም የማይጠቅምህንና የማትበላውን ገንዘብ ታደልብ ዘንድ የዚህ ዓለም ገንዘብ ያስጎመጅሃል፤ “ይሰበስባሉ፤ የሚሰበስቡለትንም አያውቁም” ብሏልና። 11 ዳግመኛም “ሐሰተኞች የአዳም ልጆች ሚዛንን ሐሰተኛ ያደርጋሉ፤ እነርሱስ መቼም መች ከከንቱ ወደ ከንቱ ይሄዳሉ” ብሏልና። 12 ሰዎች ሆይ ሚዛንንና ላዳንን በማሳበል፥ የሌላውንም ገንዘብ በመስረቅና በዐመፅ ወደ ገንዘባችሁ በመጨመር፥ የባልንጀራችሁንም ገንዘብ፥ የባልንጀራችሁንም እርሻ በመድፈር፥ ለባልንጀራችሁ ያይደለ ለራሳችሁ ትርፍ በምታደርጉት ሁሉ ዐመፅን ተስፋ አታድርጓት። 13 ይህንም ብታደርጉ እንደ ሥራችሁ ትቀበላላችሁ። 14 ሰዎች ሆይ በሚገባ በእጃችሁ ሥራ ተመገቡ እንጂ ቅሚያን አትታመኗት፤ በማይገባ ያለ ፍርድ በመቀማትና በመንጠቅ የሰውን ገንዘብ ትበሉ ዘንድ አትውደዱ። 15 ብትበሉትም አያጠግባችሁም፤ ብታደልቡትም በምትሞቱበት ጊዜ ለሌላ ትተዉታላችሁ እንጂ አይጠቅማችሁም። 16 ገንዘባችሁም ቢበዛ ልቡናችሁን አታኵሩ፤ የኀጢአተኞች ሰዎች ገንዘብ ከምድጃ እንደሚወጣ፥ ነፋስም እንደሚወስደው እንደ ጢስ ነውና፥ ከብዙ የኀጢአተኞች ገንዘብ በእውነት ያለ ጥቂት ገንዘብ ይሻላል። |