ኢሳይያስ 59:16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሰውም እንደሌለ አየ፤ የሚረዳም ሰው እንደሌለ ተረዳ፤ ሰለዚህ በክንዱ ደገፋቸው፤ በይቅርታውም አጸናቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ማንም እንደሌለ አየ፤ ወደ እርሱ የሚማልድ ባለመኖሩ ተገረመ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ ድነት አመጣለት፤ የራሱም ጽድቅ ደግፎ ያዘው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ የራሱም ጽድቅ ደገፈው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ተጨቋኞችን የሚረዳ አንድ ሰው እንኳ አለመገኘቱ አስገረመው፤ ስለዚህ እነርሱን ለማዳን በኀይሉ ተጠቅሞ ድልን እንዲጐናጸፉ አደረጋቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሰውም እንደ ሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደ ሌለ ተረዳ ተደነቀም፥ ሰለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። |
እነሆ፥ መጣሁ፤ ሰውም አልነበረም፤ ተጣራሁ፤ የሚመልስም አልነበረም፤ እጄ ለማዳን ጠንካራ አይደለምን? ወይስ ለማዳን አልችልምን? እነሆ፥ በገሠጽሁ ጊዜ ባሕርን አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋቸዋለሁ፤ ውኃም በማጣት ዐሣዎቻቸው ይሞታሉ፤ በጥማትም ያልቃሉ።
ጽድቄ ፈጥና ትመጣለች፤ ማዳኔም እንደ ብርሃን ትደርሳለች፤ አሕዛብ በክንዴ ይታመናሉ፤ ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤ በክንዴም ይታመናሉ።
እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፤ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን ማዳን ያያሉ።
እግዚአብሔር፥ “ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፤” ብሎ በጌትነቱና በክንዱ ኀይል ምሎአል።
ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ መልሰሃል፤ ለኀጢአታችንም አሳልፈህ ሰጥተኸናል።
“በኢየሩሳሌም መንገዶች ሩጡ፤ ተመልከቱም፤ ዕወቁም፤ በአደባባይዋም ፈልጉ፤ ፍርድን የሚያደርገውን እውነትንም የሚሻውን ሰው ታገኙ እንደ ሆነ ይቅር እላቸዋለሁ ይላል እግዚአብሔር።
ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው ከእነርሱ መካከል ፈለግሁ፤ ነገር ግን አላገኘሁም።