ኢሳይያስ 53:7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ተጨነቀ፥ ተሰቀየም፥ አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “እርሱ ግፍና ችግር ደረሰበት፤ ይሁን እንጂ ምንም አልተናገረም፤ ለመታረድ እንደሚወሰድ ጠቦትና በሸላቾቹ ፊት ጸጥ እንደሚል በግ ዝም አለ እንጂ ምንም አልተናገረም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፥ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። |
እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም ስለ ኀጢአታችን ለሞት አሳልፎ ሰጠው።
እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ ጠቦት በግ ሆንሁ፤ እነርሱም በእንጀራው ዕንጨት እንጨምር ስሙም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰብ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው ብለው ክፉ ምክርን እንዳሰቡብኝ አላወቅሁም ነበር።
ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤” አለው።
በማግሥቱም ዮሐንስ ወደ እርሱ ሲመጣ ጌታችን ኢየሱስን አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ የዓለሙን ኀጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።
ደግሞም ወደ ፍርድ አደባባይ ገባና ጌታችን ኢየሱስን፥ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም።
በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፤ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።