ሉቃስ 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጌታችን በጲላጦስ ፊት ስለ መቆሙ 1 ሁሉም በሙሉ ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱት። 2 እንዲህም እያሉ ይከስሱት ጀመር፥ “ይህ ሰው ለቄሣር ግብር እንዳይሰጡ ሲከለክልና ሕዝቡን ሲያሳምፅ፥ ራሱንም የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስን ሲያደርግ አገኘነው።” 3 ጲላጦስም፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ እንደ ሆንሁ አንተ አልህ” አለው። 4 ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፥ “በዚህ ሰው ላይ ያገኘሁት አንድስ እንኳ በደል የለም” አላቸው። 5 ሕዝቡም፥ “ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በመላው ይሁዳ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል” እያሉ አጽንተው ጮኹ። ጌታችን በሄሮድስ ፊት ስለ መቆሙ 6 ጲላጦስም “ገሊላ” ሲሉ ሰምቶ፤ ሰውየዉ ገሊላዊ እንደ ሆነ የገሊላን ሰዎች ጠየቀ። 7 ከሄሮድስ ግዛትም ውስጥ መሆኑን ዐውቆ ወደ ሄሮድስ ላከው፤ ሄሮድስ በዚያ ወራት በኢየሩሳሌም ነበርና። 8 ሄሮድስም ጌታችን ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ዜናውን ስለሚሰማ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይሻ ነበርና፤ የሚያደርገውንም ተአምራት ሊያይ ይመኝ ነበርና። 9 በብዙ ነገርም መረመረው፤ እርሱ ግን አንድስ እንኳ አልመለሰለትም። 10 የካህናት አለቆችና ጻፎችም ቆመው በብዙ ያሳጡት ነበር። 11 ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር አቃለለው፤ አፌዘበትም፤ የሚያንፀባርቅ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። 12 በዚያም ቀን ሄሮድስና ጲላጦስ ተስማሙ፤ ቀድሞ ጥል ነበራቸውና። 13 ጲላጦስም የካህናት አለቆችንና መኳንንቱን፥ ሕዝቡንም ጠራቸው። 14 እንዲህም አላቸው፥ “ይህን ሰው ሕዝብን ያሳምፃል ብላችሁ ወደ እኔ አመጣችሁት፤ በፊታችሁም እነሆ፥ መረመርሁት፤ ግን እናንተ ካቀረባችሁት ክስ በዚህ ሰው ላይ ያገኘሁት አንዳች በደል የለም። 15 ወደ ሄሮድስም ሰድጃችሁ ነበር፤ እርሱም ምንም ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶታል፤ ለሞትም የሚያበቃ ያደረገው ነገር የለም። 16 እነሆ፥ እኔም እንግዲህ ገርፌ ልተወው” አለ። በርባን ስለ መፈታቱና በጌታ ስለ መፈረዱ 17 በየበዓሉም ከእስረኞች አንድ ሊፈታላቸው ልማድ ነበር። 18 ሁሉም በሙሉ፥ “ይህን አስወግደው፥ ስቀለውም፥ በርባንን ግን ፍታልን” ብለው ጮሁ። 19 ያ በርባን ግን በከተማ ሁከት ያደረገና ነፍስ በመግደል የታሰረ ነበር። 20 ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታው ወድዶ፥ “ ኢየሱስን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?” ብሎ እንደ ገና ተናገራቸው። 21 እነርሱ ግን፥ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮሁ ነበር። 22 ጲላጦስም ለሦስተኛ ጊዜ፥ “ምን ክፉ ነገር አደረገ? እነሆ፥ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት አላገኘሁበትም፤ እንኪያስ ልግረፈውና ልተወው” አላቸው። 23 እንዲሰቅሉትም ቃላቸውን ከፍ አድርገው እየጮሁ ለመኑ፤ ጩኸታቸውና የካህናት አለቆች ድምፅም በረታ። 24 ጲላጦስም የለመኑት ይሆንላቸው ዘንድ ፈረደበት። 25 ያን የለመኑትን፥ ነፍስ በመግደልና ሁከት በማድረግ የታሰረውንም ሰው ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጣቸው። ወደ መስቀል ጕዞ 26 በወሰዱትም ጊዜ የቀሬና ሰው ስምዖንን ከዱር ሲመለስ ያዙት፤ ከጌታችን ከኢየሱስም በስተኋላ መስቀሉን አሸከሙት። 27 ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሴቶችም “ዋይ ዋይ” እያሉ ያዝኑለትና ያለቅሱለት ነበሩ። 28 ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። 29 መካኖች፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው የሚሉበት ወራት ይመጣልና። 30 ያንጊዜም ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ፤ ኮረብቶችንም ሰውሩን’ ይሉአቸዋል። 31 በዚህ ርጥብ ዕንጨት እንዲህ ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?” ከወንበዴዎች ጋር ስለ መሰቀሉ 32 ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችንም ከእርሱ ጋር ሊሰቅሉ ወሰዱ። 33 ቀራንዮ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜም፥ በዚያ ሰቀሉት፤ እነዚያንም ሁለት ወንበዴዎች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። 34 ጌታችን ኢየሱስም፥ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን ኣያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ፤ በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጣሉና ተካፈሉ። 35 ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር፤ አለቆችም፥ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠ ክርስቶስ ከሆነ ራሱን ያድን” እያሉ ያፌዙበት ነበር። 36 ጭፍሮችም ይዘብቱበት ነበር፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ አመጡለት። 37 እንዲህም ይሉት ነበር፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህስ ራስህን አድን።” 38 በራስጌውም ደብዳቤ ጻፉ፤ ጽሕፈቱም በሮማይስጥ፥ በጽርዕና በዕብራይስጥ ሆኖ “የአይሁድ ንጉሣቸው ይህ ነው” የሚል ነበር። ስለ ሁለቱ ወንበዴዎች 39 አብረው ተሰቅለው ከነበሩት አንዱ ወንበዴ፥ “አንተስ ክርስቶስ ከሆንህ ራስህን አድን፤ እኛንም አድነን” ብሎ ተሳደበ። 40 ጓደኛውም መልሶ ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፥ “አንተ በዚህ ፍርድ ውስጥ ሳለህ እግዚአብሔር አምላክህን አትፈራውምን? 41 በእኛስ በሚገባ ተፈርዶብናል፤ እንደ ሥራችንም ፍዳችንን ተቀበልን፤ ይህ ግን ምንም የሠራው ክፉ ሥራ የለም።” 42 ጌታችን ኢየሱስንም፥ “አቤቱ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ ዐስበኝ” አለው። 43 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ።” ጌታ ስለ መሞቱና ስለ ተአምራቱ 44 ቀትር በሆነ ጊዜም በስድስት ሰዓት ፀሐይ ጨለመ፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም ዓለም ሁሉ ጨለማ ሆነ። 45 ፀሐዩም በጨለመ ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከመካከሉ ተቀደደ። 46 ያንጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ” ብሎ ጮኸ፤ ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። 47 የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር አይቶ፥ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ”ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነው። 48 ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። 49 የሚያውቁት ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉትም ሴቶች በሩቁ ቆመው ይህን ያዩ ነበር። ጌታ ስለ መቀበሩ 50 እነሆ፥ በጎና ጻድቅ ሰው፥ የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው መጣ። 51 እርሱም በአይሁድ በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ ሀገሩም የይሁዳ ዕጣ የሚሆን አርማትያስ ነበር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን መንግሥት ተስፋ ያደርግ ነበር። 52 ወደ ጲላጦስም ሄዶ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ለመነ። 53 ሥጋውንም አውርዶ በበፍታ ገነዘው፤ ማንም ባልተቀበረበት፥ ከድንጋይም በተፈለፈለ መቃብር ቀበረው፤ ታላቅ ድንጋይም አንከባልሎ መቃብሩን ገጥሞ ሄደ። 54 ያም ቀን የሰንበት መግቢያ ዐርብ ነበር። 55 ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡ ሁለት ሴቶች ተከትለው፥ መቃብሩን፥ ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ዘይት አዘጋጁ፤ ነገር ግን በሰንበት አልሄዱም፤ ሕጋቸው እንዲህ ነበርና። |