ኢሳይያስ 30:27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነሆ፥ የእግዚአብሔር ስም ከብዙ ጊዜ በኋላ ይመጣል፤ ቍጣውም ከከንፈሮቹ ቃል ክብር ጋር ይነድዳል፤ ቃሉም ቍጣን የተመላ ነው፤ የቍጣውም መቅሠፍት እንደምትበላ እሳት ናት፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነሆ፤ የእግዚአብሔር ስም፣ ከሚነድድ ቍጣ፣ ጥቅጥቅ ካለና ከሚትጐለጐል የጢስ ደመና ጋራ ከሩቅ ይመጣል፤ ከንፈሮቹ ቍጣን የተሞሉ ናቸው፤ ምላሱም የሚባላ እሳት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነሆ፥ የጌታ ስም ከሚነድ ቁጣ፥ ከሚንቦለቦልም ጢስ ጋር ከሩቅ ይመጣል፤ ከንፈሮቹም በቁጣ የተሞሉ ናቸው፥ ምላሱም እንደምትበላ እሳት ናት፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነሆ፥ የእግዚአብሔር ኀይልና ግርማ ከሩቅ ይታያል፤ ነበልባልና ጢስ የቊጣው ምልክቶች ናቸው፤ በሚናገርበትም ጊዜ ቃሉ እንደ እሳት ይነዳል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነሆ፥ የእግዚአብሔር ስም ከሚነድድ ቍጣ ከሚትጐለጐልም ጢስ ጋር ከሩቅ ይመጣል፥ ከንፈሮቹም ቍጣን የሞሉ ናቸው፥ ምላሱም እንደምትበላ እሳት ናት፥ |
በጽዮን ያሉ ኀጢአተኞች ፈሩ፤ መንቀጥቀጥ ዝንጉዎችን ያዘ፤ እሳት እንደሚነድድ የሚነግራችሁ ማን ነው? የዘለዓለም ሀገርንስ የሚነግራችሁ ማን ነው?
ሸለቆዎችዋ ዝፍት ሆነው ይወጣሉ፤ አፈርዋም ዲን ይሆናል፤ መሬቷም በቀንና በሌሊት እንደ ዝፍት ይቃጠላል፤ ለዘለዓለምም አይጠፋም፤
በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ወንዞችም አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ። መቅሠፍትም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ኀይለኛ ፈሳሽ በቍጣ ይመጣል።
ታያላችሁ፤ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፤ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የእግዚአብሔርም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፤ ዐላውያንንም ያጠፋቸዋል።”
እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ እንደ እሳት ይመጣል፤ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ።
እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳይነድ ለአምላካችሁ ተገረዙ፤ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ።
ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፤ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
መዓቴንና የቍጣዬን ትኵሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፥ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፥ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።
ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፣ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፣ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥ እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፤ ምድርንም ከፍሬዋ፤ ጋር ትበላለች፤ የተራሮችን መሠረት ታነድዳለች።
እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ከሲና መጣ፤ በሴይርም ተገለጠልን፤ ከፋራን ተራራ፥ ከቃዴስ አእላፋት ጋር ፈጥኖ መጣ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር በቀኙ ነበሩ።