ኢሳይያስ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢሳይያስ በባቢሎን ላይ ትንቢት እንደ ተናገረ 1 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ በባቢሎን ላይ ያየው ራእይ። 2 ምድረ በዳ በሆነ ተራራ ላይ ምልክትን አቁሙ፤ ድምፃችሁንም ከፍ አድርጉባቸው፤ አለቆች በእጅ ጥቀሱ። በሮችንም ክፈቱ። 3 እኔ አዝዤ ቅዱሳኔን አመጣቸዋለሁ፤ ኀያላኔንም አመጣቸዋለሁ፤ ደስ እያላቸውም ይመጣሉ፤ ቍጣዬንም ይፈጽማሉ፤ ያዋርዱአቸዋልም። 4 በተራሮች ላይ እንደ ታላቅ ሕዝብ ድምፅ የሆነ የብዙ ሰው ድምፅ አለ። የተሰበሰቡ ነገሥታትና የአሕዛብ ድምፅም አለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ተዋጊዎች አሕዛብ ይመጡ ዘንድ አዘዘ። 5 እግዚአብሔርና የቍጣው ሠራዊት ዓለምን ያጠፉአት ዘንድ ከሩቅ ሀገር ከሰማይ ዳርቻ ይመጣሉ። 6 የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና አልቅሱ፤ ጥፋትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል። 7 ስለዚህ እጅ ሁሉ ትዝላለች፤ ሰውም ሁሉ ይደነግጣል፤ 8 ሽማግሎች ይደነግጣሉ፤ እንደምትወልድ ሴትም ምጥ ይይዛቸዋል፤ እርስ በርሳቸውም ይገዳደላሉ፤ ይደነቃሉ፤ ፊታቸውም እንደ እሳት ይንበለበላል። 9 እነሆ፥ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ፥ ኀጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ በመዓትና በጽኑ ቍጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል። 10 የሰማይም ከዋክብትና ኦሪዎን፥ የሰማይ ሠራዊትም ሁሉ ብርሃናቸውን አይሰጡም፤ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፤ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም። 11 በዓለም ሁሉ ላይ ክፋትን አዝዛለሁ፤ የኀጢአተኞችንም ኀጢአት እጐበኛለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኵራት እሽራለሁ፤ የጨካኞቹንም ኵራት አዋርዳለሁ። 12 የተረፉትም ከጥሩ ወርቅ ይልቅ የከበሩ ይሆናሉ፤ ሰውም ከሰንፔር ዕንቍ ይልቅ የከበረ ይሆናል። 13 ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣው ቀንም ሰማያት ይንቀጠቀጣሉ፤ ምድርም ከመሠረቷ ትናወጣለች። 14 የተረፉትም ሁሉ እንደ ተባረረ ሚዳቋ፥ እንደ ባዘነ በግም ይሆናሉ። የሚሰበስባቸውም የለም፤ እንዲሁም ሰው ሁሉ ወደ ወገኑ ይመለሳል፤ ሁሉም ሰው ወደ ሀገሩ ይሸሻል። 15 የተበተኑት ሁሉ ይሞታሉ፤ የተሰበሰቡትም ሁሉ በጦር ይወድቃሉ። 16 ሕፃኖቻቸውንም በፊታቸው ይጨፈጭፋሉ፤ ቤቶቻቸውንም ይበዘብዛሉ፤ ሚስቶቻቸውንም ያስነውራሉ። 17 እነሆ፥ ብር የማይሹትን፥ ወርቅም የማያምራቸውን ሜዶናውያንን በእናንተ ላይ አስነሣለሁ። 18 ፍላጾቻቸውም ጐበዞችን ይጨፈጭፋሉ፤ ሕፃኖቻችሁንም አይምሩም፤ ዐይኖቻቸውም ለልጆቻችሁ አይራሩም። 19 የመንግሥታት ክብር፥ የከለዳውያንም የትዕቢታቸው ትምክሕት የሆነች ባቢሎንም እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ትሆናለች። 20 ለዘለዓለም የሚቀመጥባት አይገኝም፤ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም፤ ዓረባውያንም በእርሷ አያልፉም፤ እረኞችም በውስጥዋ አያርፉም። 21 በዚያም የምድረ በዳ አራዊት ያርፋሉ፤ ጕጕቶችም በቤቶቻቸው ይሞላሉ፤ ሰጎኖችም በዚያ ይኖራሉ፤ በዚያም አጋንንት ይዘፍናሉ። 22 ተኵላዎችም በዚያ ያድራሉ፤ ቀበሮዎችም በሚያማምሩ አዳራሾቻቸው ይዋለዳሉ፤ ይህም ሁሉ ፈጥኖ ይሆናል፤ አይዘገይምም። |