ኢሳይያስ 30:21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ወደ ቀኝም ቢሆን ወደ ግራም ቢሆን በኋላህ በዚህ መንገድ እንሂድ የሚሉና የሚሳሳቱ ሰዎችን ድምፅ ጆሮዎችህ ይሰማሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ “መንገዱ ይህ ነው፤ በርሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ “መንገዷ ይህች ናት በእርሷም ሂድ” የሚለውን ቃል ይሰማሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከመንገድ ወጥታችሁ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ብትባዝኑ ከበስተኋላችሁ “ትክክለኛው መንገድ ይህ ነው! በዚህ ሂድ” የሚለውን ድምፅ ትሰማላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ። |
ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤ እግርህንም ከመጥፎ መንገድ መልስ። እግዚአብሔር የቀኝ መንገዶችን ያውቃልና፥ የግራ መንገዶች ግን ጠማሞች ናቸው። እርሱም መሄጃህን የቀና ያደርጋል፥ አካሄድህንም በሰላም ያሳምራል።
በመንፈስም የሳቱ ማስተዋልን ያውቃሉ፤ የሚያጕረመርሙም መታዘዝን ይማራሉ፤ ዲዳ አንደበትም ሰላም መናገርን ይማራል።”
ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ የማያውቋትንም ጎዳና እንዲረግጡ አደርጋቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህንም አደርግላቸዋለሁ፤ አልተዋቸውምም።
ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እንዲህ ይላል፥ “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ የምትሄድባትንም መንገድ እንዴት እንደምታገኝ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።
እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ከአንተ ጋር ይኖራል፤ እንደ ነፍስህም ፍላጎት ያጠግብሃል፤ አጥንትህንም ያለመልማል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፤ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች ዕወቁ፤ በእርስዋም ላይ ሂዱ፤ ለነፍሳችሁም መድኀኒትን ታገኛላችሁ፤” እነርሱ ግን፥ “አንሄድባትም” አሉ።
አገልጋዬ ሙሴ እንደ አዘዘህ ሕግን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ጽና፤ እጅግም በርታ፤ ሁሉን እንዴት እንደምትሠራ ታውቅ ዘንድ ከእርሱ ወደ ቀኝ ወደ ግራም አትበል።
እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።
ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አሳያችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይንና እግዚአብሔርን ማገልገልን በመተው እርሱን እበድል ዘንድ እግዚአብሔር ይህን አያድርግብኝ።