ዘዳግም 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዐሥሩ ትእዛዛት ( ዘፀ. 20፥1-17 ) 1 ሙሴም እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ አላቸው፥ “እስራኤል ሆይ እንድትማሩአትም፥ በማድረግም እንድትጠብቁአት ዛሬ በጆሮአችሁ የምናገራትን ሥርዐትና ፍርድ ስሙ። 2 አምላካችሁ እግዚአብሔር በኮሬብ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳኑን አጸና። 3 እግዚአብሔር ዛሬ በዚህ በሕይወት ካላችሁት ከእናንተ ከሁላችሁ ጋር እንጂ ከአባቶቻችሁ ጋር ይህችን ቃል ኪዳን አላጸናም። 4 በተራራው ላይ በእሳት መካከል እግዚአብሔር ፊት ለፊት ተናገራችሁ። 5 እኔ የእግዚአብሔርን ቃል እነግራችሁ ዘንድ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆሜ ነበር፤ እናንተ ከእሳቱ ፊት ፈርታችኋልና፥ ወደ ተራራው አልወጣችሁምና። እርሱም አለ፦ 6 “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። 7 “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። 8 “በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር ማንኛውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ 9 አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኀጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ 10 ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ። 11 “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በሐሰት አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በሐሰት የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። 12 “ዕለተ ሰንበትን ጠብቅ፤ እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህም ቀድሳት። 13 ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፥ 14 ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ እንደምታርፍ ሎሌህና ገረድህ ያርፉ ዘንድ፥ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ በሬህም፥ አህያህም፥ ከብትህም ሁሉ፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ መጻተኛ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ። 15 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ዕለተ ሰንበትን ትጠብቃትና ትቀድሳት ዘንድ አዘዘህ። 16 እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ። 17 “አታመንዝር። 18 “ነፍስ አትግደል። 19 “አትስረቅ። 20 “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፤ ምስክርንም አታሳብል። 21 “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ፤ የባልንጀራህንም ቤት፥ እርሻውንም፥ ሎሌውንም፥ ገረዱንም፥ በሬውንም፥ አህያውንም፥ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። 22 “እግዚአብሔር በተራራው ላይ፤ በእሳትና በጨለማ፥ በጭጋግና በዓውሎ ነፋስ መካከል ሆኖ በታላቅ ድምፅ እነዚህን ቃሎች ለጉባኤያችሁ ሁሉ ተናገረ፤ ምንም አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላት ላይ ጻፋቸው፤ ለእኔም ሰጣቸው። ስለ ሕዝቡ ፍርሃት ( ዘፀ. 20፥18-21 ) 23 “እንዲህም ሆነ፤ በእሳት መካከል ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፥ ተራራውም በእሳት ሲነድድ እናንተ፥ የነገዶቻችሁ አለቆች፥ ሽማግሌዎቻችሁም፥ ወደ እኔ ቀረባችሁ፤ 24 አላችሁም፦ እነሆ፥ አምላካችን እግዚአብሔር ክብሩንና ታላቅነቱን አሳይቶናል፤ ከእሳቱም መካከል ድምፁን ሰምተናል፤ እግዚአብሔርም ከሰው ጋር ሲነጋገር፥ ሰውዬው በሕይወት ሲኖር ዛሬ አይተናል። 25 አሁንም አንሙት፤ ይህችም ታላቅ እሳት አታጥፋን፤ እኛ የአምላካችን የእግዚአብሔርን ድምፅ ዳግመኛ ብንሰማ እንሞታለን። 26 ከሥጋ ለባሽ ሁሉ እኛ እንደ ሰማን በእሳት መካከል ሆኖ ሲናገር የሕያው አምላክን ድምፅ ሰምቶ በሕይወት የኖረ ማን ነው? 27 አንተ ቅረብ፤ አምላካችን እግዚአብሔር የሚለውን ሁሉ ስማ፤ እምላካችን እግዚአብሔርም ለአንተ የሚናገረውን ሁሉ ለእኛ ንገረን፤ እኛም ሰምተን እናደርገዋለን። 28 “በተናገራችሁኝም ጊዜ እግዚአብሔር የእናንተን ቃል ድምፅ ሰማ፤ እግዚአብሔርም አለኝ፦ ይህ ሕዝብ የተናገሩህን ቃል ድምፅ ሰምቼአለሁ፤ የተናገሩህ ሁሉ ትክክል ነው። 29 ለእነርሱ፥ ለዘለዓለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፥ እንዲፈሩኝ፥ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ማን በሰጣቸው፥ 30 ሄደህ፦ ወደ ቤቶቻችሁ ተመለሱ በላቸው። 31 አንተ ግን በዚህ በእኔ ዘንድ ቁም፤ ርስት አድርጌ በምሰጣቸው ምድር ላይ ያደርጉአት ዘንድ የምታስተምራቸውን ትእዛዜንና ሥርዐቴን፥ ፍርዴንም ሁሉ እነግርሃለሁ። 32 እግዚአብሔርም አምላካችሁ እንዳዘዛችሁ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። 33 በሕይወት እንድትኖሩ፥ መልካምም እንዲሆንላችሁ፥ በምትወርሱአትም ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።” |