ዕብራውያን 13:2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል ያታደሉ አሉና። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ፣ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች በዚህ ሳቢያ ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ተቀብለዋል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድን አትርሱ፤ እንደዚህ እንግዶችን እየተቀበሉ በማስተናገድ አንዳንድ ሰዎች ሳያውቁ መላእክትን ተቀብለው አስተናግደዋል። |
ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ወደ ምድር ደፍቶ ሰገደላቸው፤
ከዚህም በኋላ አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱማን አለፈ፤ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራም ይበላ ዘንድ አቆመችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር።
ለተራበውም እንጀራህን አጥግበው፤ ድሆችን ወደ ቤትህ አስገብተህ አሳድራቸው፤ የተራቈተውንም ብታይ አልብሰው፤ ከሥጋ ዘመድህ አትሸሽግ።
እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና፤ ወደ እናንተ የመጣ እንግዳ እንደ ሀገር ልጅ ይሁንላችሁ፤ እርሱን እንደ ራሳችሁ ውደዱት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።
እርስዋም ከቤተ ሰቦችዋ ጋር ተጠመቀች፤ “ለእግዚአብሔር አማኝ ካደረጋችሁኝስ ወደ ቤቴ ገብታችሁ እደሩ” ብላ ማለደችን፤ የግድም አለችን።
እኔንና አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ በእንግድነት የተቀበለ ጋይዮስም ሰላም ብሎአችኋል፤ የከተማው መጋቢ አርስጦስና ወንድማችን ቁአስጥሮስም ሰላም ብለዋችኋል።
እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥
ልጆችን በማሳደግ፥ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት፥ በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።