ዘፍጥረት 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሰዶም ኀጢአት 1 ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ወደ ምድር ደፍቶ ሰገደላቸው፤ 2 አላቸውም፥ “ጌቶች ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት ገብታችሁ እደሩ፤ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገም ማልዳችሁ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ።” እነርሱም፥ “በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም” አሉት። 3 እርሱም ግድ አላቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፤ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ቂጣንም አስጋገረላቸው፤ እነርሱም በሉ። 4 ገና ሳይተኙም የዚያች ከተማ ሰዎች፥ ታናሹም፥ ታላቁም ቤቱን በአንድነት ከበቡት። 5 ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት፥ “በሌሊት ወደ አንተ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው።” 6 ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ፊት ለፊት ወጣ፤ መዝጊያውንም በስተኋላው ዘጋው፤ 7 እንዲህም አላቸው፥ “ወንድሞች ሆይ፥ ለእናንተ አግባባችሁ አይደለም፤ በእነዚህ ላይ ክፉ አታድርጉ፤ 8 እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ላውጣላችሁ፤ እንደ ወደዳችሁም አድርጉአቸው፤ በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም በደል አታድርጉ፤ እነርሱ በቤቴ ጥላ ሥር ገብተዋልና።” 9 እነርሱም፥ “ወዲያ ሂድ፤ ከእኛ ጋር ልትኖር መጣህ እንጂ ልትገዛን አይደለም፤ አሁንም ከእነርሱ ይልቅ አንተን እናሠቃይሃለን” አሉት። 10 እጅግም ተጋፉት፤ የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ። እነዚያም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት ስበው አገቡት፤ መዝጊያውንም ዘጉት። 11 በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስክ ታላቃቸው ድረስ ዐይናቸውን አሳወሩአቸው፤ ደጃፉንም ሲፈልጉ ደከሙ፤ አጡትም። ሎጥ ሰዶምን ትቶ እንደ ወጣ 12 እነዚያም መላእክት ሎጥን አሉት፥ “ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን፥ ወንድ ልጅም ቢሆን፥ ሴት ልጅም ብትሆን፥ በዚህ ከተማ የምታውቀው ወዳጅ ቢኖርህ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው፤ 13 እኛ ይህችን ስፍራ እናጠፋታለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋትም ዘንድ እግዚአብሔር ልኮናል።” 14 ሎጥም ወጣ፤ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹም አላቸው፥ “ተነሡ፤ ከዚች ስፍራ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ያጠፋታልና።” ለአማቾቹ ግን የሚያፌዝባቸው መሰላቸው። 15 ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፥ “ተነሣ፤ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ አንተም በከተማዪቱ ሰዎች ኀጢአት እንዳትጠፋ” እያሉ ያስቸኩሉት ነበር። 16 እርሱም በዘገየ ጊዜ እነዚያ መላእክት የእርሱን እጅ፥ የሚስቱንም እጅ፥ የሁለቱን ሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ራርቶላቸዋልና። 17 ወደ ሜዳም በወጡ ጊዜ እንዲህ አሉት፥ “ራስህን አድን፤ ወደ ኋላም አትመልከት፤ አንተንም መከራ እንዳታገኝህ በዚች ሀገር በዳርቻዋና በተራራዋ አትቁም።” 18 ሎጥም አላቸው፥ “ጌቶች ሆይ፥ በጀ በሉኝ፤ 19 እነሆ፥ ባሪያህ በፊትህ ምሕረትን አግኝቼ እንደሆነ፥ ሰውነቴንም ታድናት ዘንድ፥ ቸርነትህን አብዝተህልኝ እንደ ሆነ፥ መከራ አግኝቶኝ እንዳልጠፋ ወደ ተራራ ሸሽቼ ራሴን ማዳን አልችልም። 20 እነሆ፥ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፤ እርስዋም ትንሽ ናት፤ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ራሴን ላድን፤ ሰውነቴም ከዳነች ትንሽ አይደለችም፤” 21 እርሱም አለው፥ “ስለ እርስዋ የነገርኸኝን ያችን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ፥ እንዳልኸው ልመናህን ተቀብዬሃለሁ፤ 22 እንግዲህ ፍጠንና በዚያ ራስህን አድን፤ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ሴጎር ተባለ። የሰዶምና የገሞራ መጥፋት 23 ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች፤ ሎጥም ወደ ሴጎር ገባ። 24 እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ 25 እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞችም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። 26 የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፤ የጨው ሐውልትም ሆነች። 27 አብርሃምም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ስፍራ ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤ 28 ወደ ሰዶምና ገሞራ፥ ወደ አውራጃዎችዋም ሁሉ ተመለከተ፤ እነሆም፥ ነበልባል ከምድር እንደ ምድጃ ጢስ ሲወጣ አየ። 29 እግዚአብሔርም እነዚያን ከተሞችና ሎጥ የሚኖርባቸውን አውራጃዎችዋን ሁሉ ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን ዐሰበው፤ ሎጥንም ከጥፋት መካከል አወጣው። የሞአባውያንና የአሞናውያን መወለድ 30 ሎጥም ከሴጎር ወጣ፤ ከሁለቱም ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራ ተቀመጠ፤ በሴጎር መቀመጥን ፈርቶአልና እርሱና ሁለቱ ሴቶች ልጆቹ በዋሻ ተቀመጡ። 31 ታላቂቱም ታናሺቱን አለቻት፥ “አባታችን ሽማግሌ ነው፤ በምድርም ሁሉ እንዳለው ልማድ ሊገናኘን የሚችል ሰው በምድር ላይ የለም። 32 ነዪ፥ አባታችንን ወይን እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፤ ከአባታችንም ዘር እናስቀር።” 33 በዚያችም ሌሊት አባታቸውን ወይን አጠጡት፤ ታላቂቱም ገባች፤ በዚያችም ሌሊት ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛም፥ ስትነሣም አላወቀም። 34 በነጋውም ታላቂቱ ታናሺቱን አለቻት፥ “እነሆ፥ ትናንት ከአባቴ ጋር ተኛሁ፤ ዛሬ ሌሊት ደግሞ ወይን እናጠጣው፤ አንቺም ግቢና ከእርሱ ጋር ተኚ፤ ከአባታችንም ዘር እናስቀር።” 35 አባታቸውንም በዚያች ሌሊት ደግሞ ወይን አጠጡት፤ ታናሺቱም ገብታ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛም ስትነሣም አላወቀም። 36 የሎጥም ሁለቱ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። 37 ታላቂቱም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ ይህም ከአባቴ የወለድሁት ማለት ነው። እርሱም እስከ ዛሬ የሞዓባውያን አባት ነው። 38 ታናሺቱም ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም የወገኔ ልጅ ስትል አሞን ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የአሞናውያን አባት ነው። |