ዘፍጥረት 17:17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አብርሃምም በግንባሩ ወደቀ፤ ሳቀም፤ በልቡም እንዲህ ብሎ አሰበ፥ “የመቶ ዓመት ሰው ስሆን በውኑ እኔ ልጅ እወልዳለሁን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን?” አዲሱ መደበኛ ትርጒም አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ፦ “የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን?” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አብርሃም ግንባሩ መሬት እስኪነካ ድረስ ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ ነገር ግን “ዕድሜው መቶ ዓመት የሆነው ሰው ልጅ መውለድ ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመትዋ ልጅ ልትወልድ ትችላለችን?” ብሎ በማሰብ ሳቀ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ፥ የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን? |
ሣራም በድንኳኑ ደጃፍ በስተኋላው ቆማ ሳለች ይህን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜያቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር።
ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትና ሽማግሌዎቹም ማቅ ለብሰው በግንባራቸው ተደፉ።
በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ አለ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። በአየሁም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ። የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።
እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው ተደነቁ፤ በግምባራቸውም ወደቁ።
እነርሱም በግንባራቸው ወድቀው፥ “የነፍስና የሥጋ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንድ ሰው ኀጢአት ቢሠራ የእግዚአብሔር ቍጣ በማኅበሩ ላይ ይሆናልን?” አሉ።
ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።
ዘካርያስም የእግዚአብሔርን መልአክ እንዲህ አለው፥ “ይህ እንደሚሆን በምን አውቃለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅችአለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል።”
ስለ ሠራችሁት ኀጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቈጣት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ፥ እንደ ፊተኛው በእግዚአብሔር ፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ዳግመኛ ለመንሁ፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም።
“እግዚአብሔርም፦ ያጠፋችሁ ዘንድ ስለ ተናገረ ቀድሞ እንደ ለመንሁ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ለመንሁ።
እርሱም፥ “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ፤ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ” አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና፥ “በባሪያህ ዘንድ ምን አቁሞሃል?” አለው።
ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፤ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ።
መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፤ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።
ነበልባሉም ከመሠዊያዉ ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በመሠዊያዉ ነበልባል ውስጥ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፤ በምድርም በግንባራቸው ወደቁ።