ኤፌሶን 1:7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፤ ኀጢአታችንም ተሰረየልን። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአት ይቅርታ አገኘን፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በእርሱም እንደ ጸጋው ባለጠግነት መጠን፥ በደሙ ቤዛነታችንን አገኘን፤ የበደላችንም ይቅርታ ሆነ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከእግዚአብሔር ጸጋ ሙላት የተነሣ በልጁ ደም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አገኘን። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። |
ለብዙ ሺህ ጽድቅን የሚጠብቅ፥ ቸርነትን የሚያደርግ፥ አበሳንና መተላለፍን፥ ኀጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኀጢአት በልጆች፥ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው” ሲል አወጀ።
እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን ዕወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።”
ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ በሀገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የምትመለስ አምላክ እንደ ሆንህ ዐውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።
በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም።
ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፣ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ።
ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ንስሓ ግቡ፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፤ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ትቀበላላችሁ።
አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሡ፥ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሓ እንዲመልስህ አታውቅምን?
እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ፥ በደሙም የሆነ ማስተስረያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም ከጥንት ጀምሮ በበደሉት ላይ ጽድቁን ይገልጥ ዘንድ ነው።
ዳግመናም የክብሩን ባለጠግነት ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ ለወደዳቸውና ለጠራቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የምሕረት መላእክትን ያመጣል።
እናንተም በኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ናችሁ፤ በእርሱም ከእግዚአብሔር ጥበብንና ጽድቅን፥ ቅድስናንና ቤዛነትን አገኘን።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸርነቱን ታውቃላችሁ፤ በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጸጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ባለጸጋ ሲሆን፥ ስለ እናንተ ራሱን ድሃ አደረገ።
ዐይነ ልቡናችሁንም ያበራላችሁ ዘንድ፥ የተጠራችሁበት ተስፋም ምን እንደ ሆነ፥ በቅዱሳንም የርስቱ ክብር ባለጸግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ፥
ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ ለእኔ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ አስተምር ዘንድ ይህን ጸጋ ሰጠኝ።
ዛሬ ግን እግዚአብሔር የዚህን ምክር የክብር ባለጸግነት በአሕዛብ ላይ እንዲገልጽላቸው ለፈቀደላቸው ለቅዱሳን ተገለጠላቸው፤ የምንከብርበት አለኝታችን በእናንተ አድሮ ያለ ክርስቶስ ነውና።
እናንተም በኀጢአታችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁና፥ ከእርሱ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር አላችሁ።
ይኸውም ልቡናቸው ደስ ይለው ዘንድ፥ ትምህርታቸውም በማወቅ፥ በፍቅርና ፍጹምነት ባለው ባለጸግነት፥ በጥበብና በሃይማኖት፥ ስለ ክርስቶስም የሆነውን የእግዚአብሔርን ምክር በማወቅ ይጸና ዘንድ ነው።
መድኃኒታችንም ከዐመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።
ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው።
ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዐመፀኞች አንድ ጊዜ በኀጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤
ፍቅርም እንደዚህ ነው። እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።
ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፤ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው።
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ፥ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ፤” እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።