ዘዳግም 7:19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አምላክህ እግዚአብሔር ዓይንህ እያየች፥ ታላቅ መቅሠፍትን፥ ምልክትንም፥ ተአምራትንም፥ የጸናችውንም እጅ፥ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ታላላቅ ፈተናዎችን፣ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን አምላክህ እግዚአብሔር አንተን ያወጣበትን ብርቱ እጅና የተዘረጋች ክንድ በገዛ ዐይንህ አይተሃል። አምላክህ እግዚአብሔር አሁን በምትፈራቸው ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያንኑ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዓይንህ ያየችውን ታላቅን መቅሠፍት፥ ምልክትንም፥ ተአምራትንም፥ ጌታ አምላክህ ሲያስወጣህ የጸናችውን እጅ፥ የተዘረጋውንም ክንድ፥ እንደዚሁ ሁሉ ጌታ አምላክህ አንተ በምትፈራቸው በሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደርጋል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በገዛ ዐይኖችህ ያየሃቸውን ታላላቅ መቅሠፍቶች፥ ተአምራትንና ድንቅ ሥራዎችን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክህ አንተን ነጻ ያወጣበትን ታላቅ ኀይሉንና ሥልጣኑን አስታውስ፤ ግብጻውያንን ባጠፋበት ዐይነት ዛሬ አንተ የምትፈራቸውን እነዚህንም ሕዝቦች ሁሉ ያጠፋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አምላክህ እግዚአብሔር፥ ዓይንህ እያየች፥ ታላቅን መቅሠፍት ምልክትንም ተአምራትንም የጸናችውን እጅ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፥ አስብ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል። |
ስለዚህም ፈጥነህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያንም ተገዥነት አወጣችኋለሁ፤ ከባርነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ፤ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፤
በዚያም ጊዜ ኢያሱን እንዲህ ብዬ አዘዝሁት፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥት ያደረገውን ሁሉ ዐይኖችህ አይተዋል፤ እንዲሁ በምታልፍባቸው መንግሥታት ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያደርጋል።
አምላካችን እግዚአብሔር በዐይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በታላቅም ማስፈራራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ እንደ ሆነ፥
ኢያሱም፥ “በምትወጉአቸው በጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ እንዲሁ እግዚአብሔር ያደርጋልና አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ ጽኑ፤ አይዞአችሁ” አላቸው።
እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዐይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ፥ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና።
ኢያሱም አለ፥ “ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደ ሆነ፥ እርሱም ከፊታችሁ ከነዓናዊውን፥ ኬጤዎናዊውንም፥ ኤዌዎናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ጌርጌሴዎናዊውንም፥ አሞሬዎናዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ፈጽሞ እንዲያጠፋቸው በዚህ ታውቃላችሁ።