ዘዳግም 32:47 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና፤ በዚህም ነገር ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር ዘመናችሁ ይረዝማል።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም፤ በእነርሱ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ በምትወርሷትም ምድር ረዥም ዘመን ትኖራላችሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ይህ ነገር ለእናንተ ሕይወታችሁ ነው እንጂ ከንቱ ነገር አይደለም። በዚህም ነገር ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ለመውረስ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትኖራላችሁ።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህ ሕግ የባዶ ቃላት ቅንብር አይደለም፤ እርሱ የሕይወታችሁ መሠረት ነው፤ ስለዚህ ለዚህ ቃል ታዛዦች ሁኑ፤ ይህን ብታደርጉ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሱአት ምድር ለረዥም ዘመን ትኖራላችሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና፤ በዚህም ነገር ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትቀመጣላችሁ። |
በስውር ወይም በጨለማ ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፦ በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ ጽድቅን የምናገር፥ ቅን ነገርንም የምናገር እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
በምድረ በዳ በማኅበሩ መካከል የነበረ እርሱ ነው፤ በደብረ ሲና ከአነጋገረው መልአክና፤ ከአባቶቻችንም ጋር ለእኛ ሊሰጠን የሕይወትን ቃል የተቀበለ እርሱ ነው።
ዛሬ እኔ የማዝዝህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ብትሰማ፥ አምላክህን እግዚአብሔርንም ብትወድድ፥ በመንገዶቹም ሁሉ ብትሄድ፥ ሥርዐቱንና ፍርዱንም ብትጠብቅ በሕይወት ትኖራለህ፤ በቍጥርም ትበዛለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም ልትወርሳት በምትሄድባት በምድሪቱ ሁሉ ይባርክሃል።
የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ።”
ለእናንተ፥ ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ለዘለዓለም በሚሰጣችሁ ምድር ዕድሜአችሁ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዛችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ጠብቁ።”
ጠብቁት፤ አድርጉትም፤ ይህን ሥርዐት ሁሉ ሰምተው፦ እነሆ፥ ‘ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው’ በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና፤
ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፤ አንተም ያላወቅኸውን፥ አባቶችህም ያላወቁትን መና መገበህ።
ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።