ዘሌዋውያን 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የተከለከለ ሩካቤ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 3 እንደ ተቀመጣችሁባት እንደ ግብፅ ምድር ሥራ አትሥሩ፤ እኔም ወደ እርስዋ እንደማገባችሁ እንደ ከነዓን ምድር ሥራ አትሥሩ፤ በሥርዐታቸውም አትሂዱ። 4 ፍርዴን አድርጉ፤ በእርስዋም ትሄዱ ዘንድ ሥርዐቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5 የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዐቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 6 “ከእናንተም ማንም ሰው ኀፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ሥጋ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 7 የአባትህን ኀፍረተ ሥጋና የእናትህን ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እናትህ ናትና ኀፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 8 የአባትህን ሚስት ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ኀፍረተ ሥጋ ነው። 9 የእኅትህን ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የእናትህ ልጅ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን፥ ኀፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 10 የወንድ ልጅህን ሴት ልጅ ኀፍረተ ሥጋ ወይም የሴት ልጅህን ሴት ልጅ ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአንተ ኀፍረተ ሥጋ ነውና። 11 ከአባትህ የተወለደችውን የአባትህን ሚስት ልጅ ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ ከአባትህ የተወለደች እኅትህ ናት፤ ኀፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 12 የአባትህን እኅት ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ዘመድ ናትና። 13 የእናትህን እኅት ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የእናትህ ዘመድ ናትና። 14 የአባትህን ወንድም ሚስት ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ ዘመድህ ናትና። 15 የምራትህን ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ኀፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 16 የወንድምህን ሚስት ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድምህ ኀፍረተ ሥጋ ነውና። 17 የሴትንና የሴት ልጅዋን ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድ ልጅዋን ሴት ልጅ ወይም የሴት ልጅዋን ሴት ልጅ ኀፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ አታግባ፤ ዘመዶች ናቸው፤ ኀጢአት ነውና። 18 በእኅቷ ላይ እንዳትቀና ሚስትህ በሕይወት ሳለች የእኅቷን ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ። 19 “እርስዋም በግዳጅዋ ርኵሰት ሳለች ኀፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ሳትነጻ በግዳጅዋ ወደ አለች ሴት አትቅረብ። 20 ከባልንጀራህ ሚስት ጋር አትተኛ፤ ዘርህንም አትዝራባት። 21 ከዘርህም ለሞሎክ አትስጥ የአምላክህንም ስም አታርክስ፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። 22 ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነውና። 23 ዘርህን በእርስዋ ላይ እንዳትዘራና እንዳትረክስባት ወደ እንስሳ አትሂድ፤ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት አትቁም፤ የተጠላ ነገር ነውና። 24 “ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ በእነዚህ ሁሉ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። 25 ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኀጢአቷን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፤ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች። 26 ሥርዐቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የሀገሩ ልጆች፥ በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤ 27 ከእናንተ በፊት የነበሩት የሀገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱንም አርክሰዋታልና፤ 28 ምድሪቱም ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች ባረከሳችኋት ጊዜ እናንተንም እንዳትተፋችሁ ተጠንቀቁ። 29 ከዚህ ርኵሰት ሁሉ ማናቸውን የሚያደርግ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። 30 ስለዚህ ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የሠሩትን ጸያፍ የሆነውን ወግ ሁሉ እንዳትሠሩ፥ በእርሱም እንዳትረክሱ ሥርዐቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።” |