2 ዜና መዋዕል 25:5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ንጉሡ አሜስያስም የይሁዳን ሕዝብ ሰበሰበ፤ እንደ እየአባቶቻቸውም ቤቶች አቆማቸው፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሁሉ የሽህ አለቆችንና የመቶ አለቆችን አደረገ፤ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ሁሉ ቈጠረ፤ ለሰልፍም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎችን አገኘ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም አሜስያስ የይሁዳን ሕዝብ በአንድነት ሰብስቦ፣ እንደየቤተ ሰቡ በሻለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል በመላው ይሁዳና በብንያም መደባቸው። ከዚያም ዕድሜያቸው ሃያና ከሃያ በላይ የሆናቸውን ሰብስቦ፣ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ ሆነው ጋሻና ጦር መያዝ የሚችሉ ሦስት መቶ ሺሕ ሰዎች አገኘ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አሜስያስም ይሁዳን ሰበሰበ፥ በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች ሥር እንዲሆኑ አደረገ፤ ዕድሜአቸው ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ ቈጠረ፥ ለጦርነትም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች አገኘ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ንጉሥ አሜስያስ የይሁዳና የብንያም ነገዶች የሆኑትን ወንዶች ሁሉ በየጐሣዎቻቸው በቡድን በቡድን በመደልደል በየቡድኑ በሺህ አለቆችና በመቶ አለቆች ሥር መደበ፤ በቡድን የተመደቡትም ሰዎች ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶችን ሁሉ የሚያጠቃልል ሲሆን ብዛታቸውም ሦስት መቶ ሺህ ነበር፤ እነርሱም ለጦርነት የተዘጋጁ፥ በጦርና በጋሻ አያያዝ የሠለጠኑ ምርጥ ወታደሮች ነበሩ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሜስያስም ይሁዳን ሰበሰበ፤ በእየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች እጅ በታች አቆማቸው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የይሁዳንና ብንያምን ሁሉ ቋጠረ፤ ለሰልፍም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች አገኘ። |
የእስራኤልም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆችና የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆችም ለንጉሡና ለንጉሡ ትእዛዝ ሁሉ የሚያገለግሉ ሹማምት እንደ ቍጥራቸው በየክፍላቸው እነዚህ ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሃያ አራት ሺህ ሆነው በዓመቱ ወራት ሁሉ በየወሩ ይገቡና ይወጡ ነበር።
ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ጐልማሶችን ሰበሰበ።
እርሱም የይሁዳን ሰዎች፥ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፤ ቅጥርም፥ ግንብም፥ መዝጊያም፥ መወርወሪያም እናድርግባቸው፤ ምድሪቱንም እንገዛታለን፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንደ ፈለግነው እርሱም ይፈልገናልና፤ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል፤ ሁሉንም አከናወነልን” አለ።
ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ወንጭፍ የሚወነጭፉ፥ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች ነበሩ።
ከእነርሱም ጋር ወደ ሰልፍ የሚወጡ ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሠራዊት ነበሩ፤ እነዚህም ንጉሡን በጠላቱ ላይ የሚያግዙ፥ በታላቅ ኀይል ወደ ሰልፍ የሚወጡ ጽኑዓን ነበሩ።
ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠ፤ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የአምሳም አለቆች፥ የዐሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው።
ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጡትን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቍጠሩአቸው።
ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች የአምሳ አለቆችም ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ፥ እህሉንም የሚያጭዱ፥ ፍሬውንም የሚለቅሙ፥ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ያደርጋቸዋል።