2 ዜና መዋዕል 25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)አሜስያስ መንገሡ 1 አሜስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 2 ፍጹምም ልብ ሳይኖረው አሜስያስ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። 3 መንግሥትም በጸናለት ጊዜ ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ባርያዎች ገደለ። 4 አሜስያስ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደለም ነበር ምክንያቱም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ፥ ጌታ እንዲህ ብሎ አዝዞ ነበርና፦ “ሰው ሁሉ በገዛ ኃጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች ፋንታ አይሙቱ፥ ልጆችም በአባቶች ፋንታ አይሙቱ።” ኤዶማውያን መደምሰሳቸው 5 አሜስያስም ይሁዳን ሰበሰበ፥ በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች ሥር እንዲሆኑ አደረገ፤ ዕድሜአቸው ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ ቈጠረ፥ ለጦርነትም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች አገኘ። 6 ደግሞም ከእስራኤል ዘንድ መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎችን በመቶ መክሊት ብር ቀጠረ። 7 አንድ የእግዚአብሔር ሰው ግን ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ! ጌታ ከእስራኤልና ከኤፍሬም ልጆች ጋር አይደለምና የእስራኤል ሠራዊት ከአንተ ጋር አይውጣ። 8 ብትሄድ ግን፥ በእነርሱም ማሸነፍን ብታስብ፥ የመርዳትና የመጣል ኃይል ከጌታ ዘንድ ነውና ጌታ በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል።” 9 አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሠራዊት የሰጠሁት መቶ መክሊት ምን ይሆን?” የጌታም ሰው እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ “ጌታ ከዚህ አብልጦ ሊሰጥህ ይችላል።” 10 አሜስያስም ከኤፍሬም የመጡትን ሠራዊት ወደ ስፍራቸው እንዲመለሱ ለይቶ አሰናበታቸው፤ ስለዚህም ቁጣቸው በይሁዳ ላይ ጸና፥ ወደ አገራቸውም በጽኑ ቁጣ ተመለሱ። 11 አሜስያስም በረታ፥ ሕዝቡንም አውጥቶ ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፥ ከሴይርም ልጆች ዐሥር ሺህ ገደለ። 12 የይሁዳም ልጆች ደግሞ ዐሥር ሺህ ሰዎችን በሕይወታቸው ማረኩ፥ ወደ ዓለቱም ራስ ላይ አመጡአቸው፤ እነርሱንም ከዓለቱ ራስ ላይ ጣሉአቸው፥ ሁሉም ተፈጠፈጡ። 13 አሜስያስ ግን ከእርሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ጭፍሮች ከሰማርያ ጀምረው እስከ ቤትሖሮን ድረስ በይሁዳ ከተሞች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ከእነርሱም ሦስት ሺህ ሰዎች ገደሉ፥ ብዙ ምርኮም ማረኩ። 14 አሜስያስም የኤዶማውያንን ሰዎች ከገደለ በኋላ የሴይርን ልጆች አማልክት አመጣ፥ የእርሱም አማልክት እንዲሆኑ አቆማቸው፥ ይሰግድላቸውም ያጥንላቸውም ነበር። 15 ስለዚህም የጌታ ቁጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ እንዲህ ብሎ የሚናገረውን ነቢይም ላከበት፦ “ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ያላዳኑትን የአሕዛብን አማልክት ለምን ፈለግሃቸው?” 16 እርሱም እየተናረ ሳለ ንጉሡ እንዲህ አለው፦ “በውኑ አንተ የንጉሡ አማካሪ ልትሆን ሾመነሃልን? ተው፤ እንዲገድሉህ ለምን ትሻለህ?” ነቢዩም፦ “ይህን አድርገሃልና፥ ምክሬንም አልሰማህምና ጌታ ሊያጠፋህ እንዳሰበ አወቅሁ” ብሎ ተወ። እስራኤል ይሁዳን ድል መንሣቱ 17 የይሁዳም ንጉሥ አሜስያስ ተማክሮ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ኢዮአስ እንዲህ ብሎ ላከ፦ “ና፥ እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ።” 18 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮስያስ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ እንዲህ ብሎ ላከ፦ “የሊባኖስ ኩርንችት፦ ‘ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው’ ብሎ ወድ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኩርንችቱን ረገጠ። 19 አንተም፦ ‘እነሆ፥ ኤዶምያስን መትቻለሁ’ ብለህ ኰርተሃል፤ በቤትህ ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር አብረህ ለመውደቅ ለምን መከራ ትሻላህ?” 20 የኤዶምያስንም አማልክት ስለ ፈለጉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው የጌታ ፈቃድ ነበረና አሜስያስ አልሰማም። 21 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤት-ሳሚስ ላይ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 22 ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፥ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 23 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤት-ሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 24 ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በጌታም ቤት ከዖቤድኤዶም ጋር የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ የንጉሡም ቤት መዛግብት፥ በመያዣ የተያዙትንም ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ። አሜስያስ መሞቱ 25 የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከኢዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 26 የቀረውም የፊተኛውና የኋላኛው የአሜስያስ ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 27 አሜስያስም ጌታን ከመከተል ከራቀ በኋላ በኢየሩሳሌም ሤራን አሤሩበት፥ ወደ ለኪሶም ኰበለለ፤ ከኋላውም የሚከታተሉትን ሰዎች ወደ ለኪሶ ላኩበት፥ በዚያም ገደሉት። 28 በፈረስም ጭነው አመጡት፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት። |