1 ሳሙኤል 17:12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፤ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፤ ስምንት ልጆችም ነበሩት፤ እሴይም በሳኦል ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ዳዊት በይሁዳ የቤተ ልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዳዊት፥ በይሁዳ ስምንት ወንዶች ልጆች የነበሩት፥ የቤተልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይም በሳኦል ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ዳዊት በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም የሚኖር የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር፤ እሴይ ስምንት ልጆች ያሉት ሲሆን ሳኦል በነገሠበት ዘመን በዕድሜ የገፋ ሽማግሌ ሰው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፥ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፥ ስምንትም ልጆች ነበሩት፥ በሳኦልም ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። |
የዳዊትም የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደረገው፥ የያዕቆብም አምላክ የቀባው፥ የታማኙ ሰው፥ በእስራኤል ዘንድ መልካም ባለመዝሙር የሆነው፥ የታማኙ የእሴይ ልጅ የዳዊት ንግግር ይህ ነው፤
አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፥ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።
ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
የሰውዮውም ስም አቤሜሌክ፥ የሚስቱም ስም ኑኃሚን፥ የሁለቱም ልጆች ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበረ፥ የቤተ ልሔም ይሁዳም የኤፍራታ ሰዎች ነበሩ። ወደ ሞዓብም ምድር መጡ በዚያም ተቀመጡ።
ሴቶችም ጎረቤቶችዋ፥ ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት እያሉ ስም አወጡለት፣ ስሙንም ኢዮቤድ ብለው ጠሩት። እርሱም የዳዊት አባት የእሴይ አባት ነው።
በተራራማው በኤፍሬም ሀገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። ስሙም፥ የናሲብ ልጅ የቴቆ ልጅ፥ የኤልዩ ልጅ ፥ የኢያርምያል ልጅ፥ ኤፍራታዊው ሕልቃና ነበረ።
እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? የዘይቱን ቀንድ ሞልተህ ና፤ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቼአለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ” አለው።
ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፥ “እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና ሲመታ የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፤ ሰውየውም ጠቢብ፥ ተዋጊም ነው፤ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” አለ።