Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዳዊትና ጎልያድ

1 ፍልስጥኤማውያን ሠራዊታቸውን ለጦርነት አሰባስበው፥ በይሁዳ ምድር በሰኮ ላይ አከማቹ፤ በሰኮና በዓዜቃ መካከል ባለው በኤፌስደሚምም ሰፈሩ።

2 ሳኦልና እስራኤላውያን ደግሞ ተሰብስበው በዔላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ተሰለፉ።

3 በመካከላቸው ሸለቆ ሆኖ፥ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ተራራ እስራኤላውያን ደግሞ ሌላውን ተራራ ያዙ።

4 ከጋት ከተማ የመጣ፥ ቁመቱ ስድስት ክንድ ከስንዝር የነበር ጎልያድ ተብሎ የሚጠራ አንድ ግዙፍ ዋነኛ ጀግና ሰው፥ ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ።

5 እርሱም ከናስ የተሠራ የናስ ቁር ደፍቶ፥ ክብደቱ አምስት ሺህ ሰቅል የሆነ የናሐስ ጥሩርም ለብሶ ነበር።

6 በእግሮቹም ላይ የሐናስ ገምባሌ አድርጎ፥ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናሐስ ጭሬ ይዞ ነበር።

7 የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፥ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር።

8 ጎልያድ ቆሞ ለተሰለፈው የእስራኤል ሠራዊት እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፤ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ መውጣታችሁ ስለ ምንድነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተም የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁምን? አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤

9 ከእኔ ጋር ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፥ እኛ ባርያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባርያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ።”

10 ከዚያም ፍልስጥኤማዊው፥ “ዛሬ የእስራኤልን ሠራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ” አለ።

11 ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም።

12 ዳዊት፥ በይሁዳ ስምንት ወንዶች ልጆች የነበሩት፥ የቤተልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይም በሳኦል ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር።


ዳዊት በሳኦል ጦር ሰፈር

13 ሦስቱ የእሴይ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነት ሄደው ነበር፤ እነርሱም ታላቁ ኤሊአብ፥ ሁለተኛው አሚናዳብ፥ ሦስተኛውም ሻማ ይባላሉ፤

14 ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤

15 ዳዊት ግን የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተልሔም ይመላለስ ነበር።

16 ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጠዋትና ማታ እየመጣ በመቆም ይታያቸው ነበር።

17 በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ።

18 ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለሻለቃው የጦር አዛዥ አብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደ ሆኑ አይተህ፥ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ።

19 እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው በዔላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ ናቸው።”

20 ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፥ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጉዞ ጀመረ። ልክ ሠራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ።

21 እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር።

22 ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ።

23 ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፥ እነሆ፥ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ ዳዊት ሰማ።

24 እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሃት ከፊቱ ሸሹ።

25 እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፥ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፥ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር።

26 ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፥ “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ።

27 እነርሱም፥ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት።

28 ታላቅ ወንድሙ ኤሊአብ፥ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ፥ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውካቸው? ዕብሪትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው።

29 ዳዊትም፥ “እኔ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልምን?” አለ።

30 ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፥ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤

31 ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው።

32 ዳዊትም ሳኦልን፥ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ እኔ አገልጋይህ ሄጄ እዋጋዋለሁ” አለው።

33 ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና ልጅ ነህ፥ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለሆነ፥ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው።

34 ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፥ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፥

35 ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር።

36 ባርያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል።

37 ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ ጌታ አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሲል ዳዊት ተናገረ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ ጌታ ካንተ ጋር ይሁን!” አለው።

38 ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ከናሐስ የተሠራ ቁር ደፋለት፤ ጥሩርም አለበሰው።

39 ዳዊትም ይህን ዓይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፥ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤ እርሱም ሳኦልን፥ “ያልተለማመድሁት ስለሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ያንን አወለቀው።

40 ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኮረጆው ከጨመረ በኋላ፥ ወንጭፉን በእጁ ይዞ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ።


ዳዊት ጎልያድን ድል ማድረጉ

41 ፍልስጥኤማዊውም፥ ጋሻ ጃግሬውን ከፊት ከፊቱ በማስቀደም፥ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ።

42 እርሱም ዳዊትን ትኩር ብሎ ሲያየው፥ ደም ግባት ያለው፥ መልከ መልካምና ልጅ ነበር፤ ስለዚህ በንቀት ዐይን ተመለከተው።

43 ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው።

44 እርሱም ዳዊትን፥ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፥ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው።

45 ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሠራዊት አምላክ በሆነው፥ ሁሉን በሚችል በሠራዊት ጌታ ስም እመጣብሃለሁ።

46 ጌታ ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቆርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፤ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ እግዚአብሔር መኖሩን ያውቃል።

47 እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ ጌታ ያለ ሰይፍ ወይም ያለ ጦር እንደሚያድን ያውቃሉ፤ ሰልፉ የጌታ ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።”

48 ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፥ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ።

49 እጁንም ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ በግምባሩም ምድር ላይ ተደፋ።

50 በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም።

51 ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ።

52 ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እየፎከሩ ፍልስጥኤማውያንን እስከ ጋት መግቢያና እስከ ዔቅሮን በሮች ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያንም ሬሳ ከሸዓራይም አንሥቶ እስከ ጋትና ከዚያም እስከ ዔቅሮን በሮች ባለው መንገድ ላይ ወደቀ።

53 እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን አሳደው ተመለሱ፤ ሰፈራቸውንም በዘበዙ።

54 ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የጦር መሣሪያዎቹን ግን በራሱ ድንኳን ውስጥ አስቀመጠ።


ዳዊት ወደ ሳኦል መቅረቡ

55 ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ለመግጠም ሲሄድ ሳኦል ተመልክቶ የሠራዊቱን አዛዥ አበኔርን፥ “አበኔር ሆይ፤ ይህ ልጅ የማን ነው?” ሲል ጠየቀው። አበኔርም፥ “ንጉሥ ሆይ፤ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አላውቅም” ብሎ መለሰለት።

56 ንጉሡም፥ “እንግዲህ ወጣቱ የማን ልጅ እንደሆነ ተከታትለህ ድረስበት” አለው።

57 ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ እንደ ተመለሰ፥ አበኔር ይዞ ንጉሡ ዘንድ አቀረበው። በዚህ ጊዜ ዳዊት የጎልያድን ራስ በእጁ ይዞ ነበር።

58 ሳኦልም “አንተ ወጣት የማን ልጅ ነህ?” ብሎ ጠየቀው። ዳዊትም “የቤተልሔም ነዋሪ የሆነው የአገልጋይህ የእሴይ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰለት።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos