ዘፍጥረት 35 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ያዕቆብን እንደ ባረከው 1 እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው፥ “ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፤ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጥሁልህ ለእኔ መሥውያን ሥራ።” 2 ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ፥ “ከእናንተ ጋር ያሉ እንግዶች አማልክትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ንጹሓንም ሁኑ፤ ልብሳችሁንም እጠቡ፤ 3 ተነሡና ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ቀን ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው፥ ከመከራም አድኖ ላሻገረኝ ለእግዚአብሔር መሠውያን እንሥራ።” 4 በእጃቸው ያሉትንም እንግዶች አማልክት ሁሉ፥ በጆሮአቸውም ያሉትን ጉትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴቄም አጠገብ ካለችው ዛፍ በታች ቀበራቸው። እስከ ዛሬም ድረስ አጠፋቸው። 5 እስራኤልም ከሴቄም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም መፍራት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፤ የእስራኤልንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም። 6 ያዕቆብም እርሱ፥ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ፤ እርስዋም ቤቴል ናት። 7 በዚያም መሠውያዉን ሠራ፤ የዚያንም ቦታ ስም ቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ከዔሳው ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና። 8 የርብቃ ሞግዚት ዲቦራም ሞተች፤ ከቤቴል በታች ባላን በሚባል ዛፍ ሥርም ተቀበረች፤ ያዕቆብም ስሙን “የልቅሶ ዛፍ” ብሎ ጠራው። 9 እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደገና በሎዛ ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም ባረከው። 10 እግዚአብሔርም አለው፥ “ስምህ ያዕቆብ አይባል፤ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ” ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። 11 እግዚአብሔርም አለው፥ “አምላክህ እኔ ነኝ፤ ብዛ፤ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፤ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። 12 ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ።” 13 እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። 14 ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፤ ዘይትንም አፈሰሰበት። 15 ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ “ቤቴል” ብሎ ጠራው። የራሔል ሞት 16 ያዕቆብም ከቤቴል ተጓዘ፤ በጋዲር ግንብ አጠገብ ድንኳን ተከለ፤ ወደ ኤፍራታም ለመድረስ በቀረበ ጊዜ ራሔልን ምጥ ያዛት፤ በምጡም ተጨነቀች። 17 በምጥ ሳለችም አዋላጂቱ፥ “አትፍሪ ይህኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንልሻልና” አለቻት። 18 ከዚያም በኋላ ነፍስዋ ልትወጣ ደረሰች፤ ሞትዋ በእርሱ ሆኖአልና ስሙን የጭንቀቴ ልጅ ብላ ጠራችው ፤ አባቱ ግን ብንያም አለው። 19 ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታም በምትወስድ መንገድ ተቀበረች፤ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት። 20 ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፤ እርስዋም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ትባላለች። 21 ከዚህም በኋላ እስራኤል በዚያች ምድር ሳለ ሮቤል ሄደ፤ ከአባቱ ከያዕቆብ ዕቅብት ከባላ ጋርም ተኛ፤ እስራኤልም ሰማ። በፊቱም ክፉ ነገር ሆነ። የያዕቆብ ልጆች ( 1ዜ.መ. 2፥1-2 ) 22 የያዕቆብም ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው፤ 23 የልያ ልጆች፤ የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤ 24 የራሔል ልጆች፤ ዮሴፍ፥ ብንያም፤ 25 የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆችም፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤ 26 የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆችም፤ ጋድ፥ አሴር፤ እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው። የይስሐቅ ሞት 27 ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ፥ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት በአርባቅ ከተማ ወደምትገኘው ወደ መምሬ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ። 28 የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ። 29 ይስሐቅም ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተጨመረ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት። |